የኢትዮ ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው

56

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2012(ኢዜአ) ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የኢትዮ ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ተጀምሯል።

የምክክር መድረኩን የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኦማር በሽር ማኒስ የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ተከፍቷል።

ከመክፈቻ ንግግሩ በኋላ በተካሄደው ውይይት በድንበር አካባቢ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መረጃ ተለዋውጧል፤ በሁለቱ አገራት በድንበር አካባቢ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን በትብብር መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያም ትኩረት አድርገው መክረዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ከዚህ ቀደም የተቋቋሙት የተለያዩ የድንበር ኮሚቴዎች እና የትብብር ማዕቀፎችን አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት መደገሩም ተገልጿል።

በነገው እለትም አጀንዳውን በመቋጨት በሁለቱ ቀናት በተደረገው ምክክር የተደረሱ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ በኩል የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ ጄኔራል አደም መሀመድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዲሁም የመረጃ እና ደህንነት፣ የፌደራል ፖሊስ እና ሌሎች ከፍተኛ የጸጥታና ደህንነት ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በተመሳሳይ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስማ ሙሀመድ አብደላህን ጨምሮ የሱዳን የመከላከያ እና የደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም