በጋሞ ዞን በበልግ እርሻ ከ90 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፈነ

69

አርባ ምንጭ ግንቦት 8/2012 (ኢዜአ) በጋሞ ዞን እየተካሄደ ባለው የበልግ አዝመራ እንቅስቃሴ ከ90 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ገለጸ።

በዘር የተሸፈነው መሬት  በዞኑ በሚገኙ 14  በልግ አብቃይ ወረዳዎች ነው።

የመምሪያው ምክትል  ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ሙላቱ ለኢዜአ እንዳሉት መሬቱ በበልግ ከለማው ውስጥ  ከ55 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው ዋና ዋና ሰብል የሆኑት በቆሎ፣ ማሽላ፣ ቦሎቄና ድንች ይገኙበታል።

ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ 28 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ መሰራጨቱን ጠቅሰዋል።

በልማቱ እየተሳተፉ ካሉት 185 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መካከል  14 ሺህ 396ቱ ሴቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ መዘናጋት እንዳይኖር ለአርሶ አደሩ  አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እየተደረገለት  መሆኑንም አቶ ማቴዎስ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ  ማሣውን  አራት ጊዜ በማረስ በአግባቡ እንዲያለሰልስ የቅርብ  ድጋፍ  ማድረጋቸውን  የተናገሩት ደግሞ  በምዕራብ ዓባያ ወረዳ የዋንካ ዋጅፎ ቀበሌ የልማት ጣቢያ  ባለሙያ አቶ ዓለሙ ቶማ ናቸው።

በተለይ ከቴክኖሎጂ  አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አርሶ አደሩ ሙሉ ፓኬጅ ተጠቅሞ ምርታማ እንዲሆን  እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዚሁ ቀበሌ  አርሶ አደር ካልሳ ያሱማ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የበረሃ አንበጣ የተከሰተ ቢሆንም ብዙም ጉዳት ሳያደርስ በባህላዊ መንገድ በመከላከል ማባረር እንደቻሉ  ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ እንደገለጹት በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ በመስመር የዘሩት የበቆሎ  ቡቃያ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝና በአግባቡ በመኮትኮት እየተንከባከቡ ነው።

የኮሮና  ወረርሽኝ  ተከትሎ ከዚህ በፊት በደቦ ተጋግዘው ሲያለሙ የነበረውን ሁኔታ ዘንድሮ በማስቀረት በግላቸው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በካምባ ወረዳ የባልታ ባኮ ቀበሌ አርሶ አደር ዳንኤል ዳይታ ናቸው።

ጥንቃቄ በማድረግ የቤተሰብ ጉልበትንና የቀን ሠራተኛ በመቅጠር ባላቸው ሁለት ሄክታር ከግማሽ  ማሳቸው ላይ  ስንዴ፣ ባቄላና ድንች እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም