ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

112

ሀዋሳ ግንቦት 8/2012 (ኢዜአ) የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን በማጠናከር የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

ከደቡብ ክልል ለግድቡ ግንባታ ዘንድሮ  45 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡም ተመልክቷል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የደቡብ ሬዲዮ ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኛ ሄኖክ አበራ እንዳለው ግብጾች ዓባይን የሕይወታቸው አካል አድርገው ያያሉ።

ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያላቸው አቋም የራስን ጥቅም መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተናግሯል።

በአሁኑ ወቅት ግብጾች ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ተገቢነት እንደሌለውና የራስን ጥቅም ብቻ መሠረት ያደረገ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውያን ይህን በማውገዝ ለግንባታ ሥራው የሚጠበቅብንን ማበርከት ይገባናል ብሏል።

አቶ አንዷለም አብርሃም በበኩላቸው ግብፅ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የያዘችው አቋም የተዛባና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ የጣሰ መሆኑን ገልጸዋል።

"የሕዳሴ ግድብ የህልውናችን መሠረትና የኢትዮጵያ ው ያን ማንነት መገለጫ ነው" ያሉት አቶ አንዷለም ለግድቡ ግንባታ በተደጋጋሚ ቦንድ በመግዛት የሚጠበቅባቸውን ሲወጡ እንደቆዩ አስታውሰዋል።

"እኛም በዘር፣ በኃይማኖት፣ በብሔርና ፖለቲካ ሳንከፋፈል አንድ እንድንሆን ያደረገንን የሕዳሴ ግድብ ከፍጻሜ ለማድረስ አንድ ሆነን መቀጠል አለብን" ብለዋል።

የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው በጋራ እንዲቆሙ ማድረግ የቻለ ታላቅ ሀብት በመሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ በማድረግ ለፍጻሜ እንዲበቃ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ ሌላ አስተያየት ሰጪ አቶ ረታ አይዛ ናቸው።

ቀድሞ ሲል ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ እንደነበር ጠቁመው አሁንም ባላቸው የመካኒክነት ሙያ ተጠቅመው ለግድቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚኪያስ እሥራኤል በበኩላቸው "የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ሳይስተጓጎል እንደቀጠለና የግብፅ አቤቱታም ሆነ የኮሮና ቫይረስ ክስተት በግድቡ ግንባታ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አይኖርም" ብለዋል።

ግብፅ ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው ቅሬታ የዲፕሎማሲያዊም ሆነ የጋራ ተጠቃሚነት መስፈርት መሠረት ያላደረጋ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ በግድቡ ውኃ ሙሌት ዙሪያ የያዘችውን አቋም አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት የክልሉ ሕዝብ በቦንድ ግዥ፣ የደረት ላይ ምልክት ሽያጭና የ8100 የሞባይል መልዕክት በማስተላለፍ የሚጠበቅበትን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን 45 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብስቡንም አቶ ሚኪያስ አመልክተዋል።

የክልሉ ኅብረተሰብ ባለፉት ዓመታት ከአንድ ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም