የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 27 ፓርቲዎችን ሰረዘ

111

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 27 ፓርቲዎች መሰረዙን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ቦርዱ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በቀድሞ ህግ ሰርተፍኬት የነበራቸው እና በቀድሞው ህግ ምዝገባ ጀምረው ለነበሩ 106 ፓርቲዎች በአዲሱ ህግ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ በደብዳቤ ማሳወቁንም ጠቅሷል፡፡

ከቦርዱ ደብዳቤ ከደረሳቸው 106 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 76 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶችን ያቀረቡ ሲሆን በሕጉ መሠረት ተሟልቶ የቀረበ ስለመሆኑ እየተመረመረ መሆኑ ተገልጿል።

በምርመራውም፡-

• ፓርቲዎቹ በደብዳቤ የተገለጸላቸውን ነጥቦች ሁሉንም ማሟላታቸውን ማረጋገጥ ( የህገደንብ ለውጥ ጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች አቀራረብ፣ የመስራቶች ፊርማ … የመሳሰሉት)

• የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጉ መሠረት ማሟላት የሚገባቸውን የመሥራች አባላት ብዛት ትክክለኛነትን ለመፈተሽ ካቀረቡት የመሥራች አባላት ዝርዝር ናሙና የማውጣት

• ናሙናዎቹ በትክክል ግለሰቦቹ የተፈረሙ መሆናቸውን ወደተፈረሙበት ቦታ በመላክ ማረጋገጥና

• የህገ ደንብ ለውጦችና፣ የጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች በትክክል መያያዛቸውን ማረጋገጥን እንደሚያጠቃልልም ቦርዱ ገልጿል።

ሰነዶቻቸውን ካስገቡት 76 ፓርቲዎች መካከል ምን ያህሎቹ መስፈርት እንዳሟሉም በቦርዱ ይፋ የሚደረግ ይሆናልም ተብሏል።

ነገር ግን የሚጠበቅባቸውን ሰነድ ማስገባት ያልቻሉ እና ጊዜ እንዲራዘምላቸው የጠየቁ 15 የፓለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ ከነዚህ ፓርቲዎች መካከል ከስር የተጠቀሱት የ13ቱ አጥጋቢ ምክንያት ባለማቅረባቸው እንዲሰረዙ ቦርዱ መወሰኑን ገልጿል።

የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ሳያገኙ የተሰረዙ ፓርቲዎች፡ -

1. የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ

2. የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ) - የመስራች አባላት
ዝርዝር ያላቀረበ

3. የየም ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ( የብዴን) - የመስራች
አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ

4. የደንጣ ዱባሞ ክችንችላ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት -
የመስራች አባላት ዝርዝርም ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ

5. የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ ( ኮንግረስ) - የመስራች
አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

6. የትግሪ ወርጂ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ( ትወብዴድ) -
ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ

7. የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) - የመስራች አባላት
ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤም ያላካሄደ

8. የኢትዮጵያን አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢአዴድ) -
ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ

9. የመላው አማራ ህዝብ ፓርቲ (መዐሕፓ) - የመስራች አባላት
ዝርዝር ያላቀረበ

10. የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) - የመስራች
አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

11. የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ ( ደቡብ ኮንግረስ) -
የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

12. የሸኮና አካባቢው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሸአሕዲድ)
-ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ

13. ነጻነትና ሰላም ለኢትዮጵያ ህብረት ፓርቲ ( ነጻነትናሰላም) -
የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

በሌላ በኩል ሌሎች 14 ፓርቲዎች ደግሞ ከቦርዱ በተደረገው ጥሪ መሰረት ሰነዶቻቸውን ከነአካቴው ያላቀረቡ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መዋሃዳቸውን መግለጻቸውን እና ይህ በመሆኑም 14ቱ ፓርቲዎች እንዲሰረዙ ቦርዱ መወሰኑን ይፋ አድርጓል።

ሰነድ ባለማምጣታቸው እንዲሰረዙ የተሰወኑት ፓርቲዎች ፡-

1. የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ
2. መላው ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
3. የከምባታ ሕዝቦች ኮንግረስ
4. የሐድያ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
5. የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት
6. የዲል ወቢ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ
7. የቤንች ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት
8. የስልጤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
9. የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ
10. የሱማሌ አንድነት ፓርቲ
11. ነፃነት ለአንድነትና ለፍትሕ ፓርቲ
12. ብሔራዊ ተሀድሶ ለሰላም ልማት
13. የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት
14. የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ ሲሆኑ ፣

ሁለት ፓርቲዎች ሰነዶችን ማቅረብ አለመቻላቸው በፓርቲው የውስጥ ችግር የተነሳ መሆኑ ስለታመነበት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን የኮቪድ-19 ወረርሽን በሚያበቃበት ወቅት አንዲያከናውኑ ቦርዱ ሲወስን ሌሎች ሰነዶቻቸው ግን ከላይ በተጠቀሰው መንገድ እየተገመገሙ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።

በልዩ ሁኔታ የሰነድ ካስገቡ ፓርቲዎች ጋር ሰነዶች እንዲታይላቸው የተደረጉ ፓርቲዎች፡-

1. ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ( ኢዴፓ)
2. ወለኔ ህዝቦች ፓርቲ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም