ትራንስ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል እንደርታ ወረዳ የአካባቢ ጥበቃ ስራን እያገዘ ነው

79
መቀሌ ሰኔ 28/2010 ትራንስ ኢትዮጵያ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በትግራይ ክልል እንደርታ ወረዳ ከሁለት አመት በፊት የጀመረው የአከባቢ ጥብቃ ስራ  ውጤት እያመጣ መሆኑ የወረዳው ግብርናና ገጠር ልማት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። በወረዳው ግብርናና ገጠር ልማት ጽሕፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ብርሀኑ ታደለ እንደገለጹት ትራንስ ኢትዮጵያ በአከባቢ ጥበቃ ድጋፍ ለማድረግ ያሳየው ጅምር የሚበረታታ ነው። ማህበሩ የተጎዱ  አካባቢዎችን እንዲያገግሙ ለማድረግ  ህብረተሰቡን በክፍያ በማሰራት  ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ወጭ አድርጓል። “በዚህም ማህበሩ ለማልማት ከያዘው 300 ሄክታር ከሚሸፍነው ‘የገረብ ጨአ’ ተፋሰስ  ውስጥ በ160 ሄክታር መሬት የተለያዩ የእርከን ስራዎችና የችግኞች ተከላዎች ተካሂደዋል” ብለዋል፡፡ ቀሪውን መሬት በተመሳሳይ መንገድ ለማልማት የማህበሩ ድጋፍ እንዳይለያቸውም ጠይቀዋል፡፡ የትራንስ ኢትዮጵያ አክስዮን ማህበር ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መውጫ ወልዱ በበኩላቸው አክስዮን ማህበሩ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ላይ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል። አክስዮን ማህበሩ እያደረገ ያለውን የኮርፕሬት ሀላፊነትና ማህበራዊ አገልግሎት ለሰራተኞቹ  ቀደም ሲል ያስጎበኘ ሲሆን ከአሁን በፊትም ቆላ ተምቤን ዶክተር አታክልቲ ቀበሌ ተመሳሳይ ስራ አከናውኖ ለህብረተሰቡ ማስረከቡን አስታውቀዋል። በእንደርታ ወረዳ የድድባ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪው አርሶ አደር ካህሱ ሀይሉ እንደገለጹት አከባቢው ከጥቂት ዓመታት በፊት በጣም የተጎዳና ለአፈር መከላት የተጋጠ ነበር ፡፡ ከእንስሳትና ከሰው ንኪኪ ውጭ ከመደረጉም በተጨማሪ የተለያዩ የውሀ ማቆሪያና የእርከን ስራዎች በማከናወን አከባቢው ወደ ቀድሞ ይዞታው እየተመለሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠፍተው የነበሩ አገር በቀል ዛፎችም ዳግም ማቆጥቆጥ መጀመራቸውን በመግለጽ “ከተፋሰሱ ስር የሚገኝ የእርሻ መሬት በጎርፍ ከመወሰድ ድኗል” ብለዋል፡፡ አካባቢው ከእንስሳትና ከሰው ንኪኪ ውጭ ለማድረግና ከህብረተሰቡ ይሁንታ ለማግኘት ለአንድ አመት ያህል ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ ሴት አርሶ አደር የጥምውሀ መሓሪ ናቸው። ውይይቱን ተከትሎ ላለፉት ሁለት አመታት የተለያዩ የእርከን ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው በአጭር ጊዜ ውስጥ የእጽዋት ሽፋኑ ከመጨመሩ ባለፈ ሳር እያጨዱ ለመጠቀም እንደቻሉም ተናግረዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም