"ቅኔ ነው አገር" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ህብረ ዜማ ተመረቀ

101

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2012 (ኢዜአ) በሙዚቃ ባለሙያው እዮኤል መንግስቱ ተዘጋጅቶ አንጋፋ እና ተተኪ ድምጻውያን የተሳተፉበት "ቅኔ ነው አገር" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ህብረ ዜማ ትናንት ማምሻውን ተመርቋል።

በአርቲስቱ የሠራውን ህብረ ዜማ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ አስረክቧል።

በህብረ ዜማው ላይ ከአንጋፋዎቹ አርቲስቶች መካከል ነዋይ ደበበ፣ ጸጋዬ እሸቱና ታደለ በቀለ ያሉበት ሲሆን፤ከተተኪዎቹ ማህሌት ነጋሽ፣ የማርያም ቸርነትና ይድነቃቸው ገለታ ይገኙበታል።

በድምጻዊያኑ ሥራ ላይ የሙዚቃ ባለሙያው ሰርጸ ፍሬስብሃት እና ዶክተር እዝራ አባተን ጨምሮ አንጋፋና ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ የፊልምና የምስል ቅንብር ባለሙያዎች እንዲሁም ተዋንያን እንደተካፈሉበትም ነው የተገለጸው። 

የሙዚቃ ሥራውን ለማጠናቀቅ የአንድ ወር ጊዜ እንደፈጀም ተመልክቷል።

የሙዚቃ ሥራው ዋንኛ መልዕክት በችግር ጊዜ መተሳሰብና መረዳዳት እንዲሁም በጋራ መቆም ከተቻለ አገርን ወደ ተሻለ ሁኔታ ማሻገር እንደሚቻል የሚያሳይ ነው ተብሏል።

የሙዚቃ ባለሙያው ሰርጸ ፍሬስብሃት በዚህ ጊዜ ''አባቶቻችን ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የገጠሟትን ፈተናዎች በመተባበርና በመተጋጋዝ ለችግሮቿ መፍትሄ አበጅተው አልፈዋል'' ብሏል።

ይሄም ትውልድ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የመጣውን አዲስ ፈተና በተባበበረ ክንድ እንድታልፍ የማድረግ ታሪካዊ ሃላፊነት እንደተጣለበት ገልጿል።

ትውልዱ እንዲህ አይነት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሲያጋጥም ሰው ሆኖ የመገኘትና ለችግር ደራሽ ሆኖ የመቆም ሃላፊነት እንዳለበት አመልክቷል።

ህብረ ዜማውም ይህንን መልዕክት የሚያስተላልፍ እንደሆነ ጠቁሟል።

የሙዚቃ ሥራው በአጠቃላይ ኪነ ጥበብ ለሰዎች መልዕክትን በቀላሉ ማስተላለፍና ማስረጽ እንደምትችል የሚያሳይ እንደሆነም ተናግሯል።

የህብረ ዜማው አዘጋጅና ዳይሬክተር እዩኤል መንግስቱ በበኩሉ፤ የዜማው መልዕክት አገርን በቃል ብቻ መውደድ ሳይሆን 'አገር መውደድ የሚፈተነው በችግሯ ጊዜ ስንቆምላት ነው' የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሆነ ገልጿል።

በኮሮናቫይረስ ከሚደርሰው የጤና ጉዳት ባለፈ በሽታው በሰዎች ኑሮ ላይ የሚያደርሰው ማህበራዊ ጫና ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያሻው ተናግሯል።

ህብረ ዜማው በተለያየ ዘመናት የነበሩ ሶስት ትውልዶችን ያገናኘ የሙዚቃ ሥራ እንደሆነ ነው አርቲስቱ የገለጸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ''ህብረ ዜማው ዘመንን አልፎ ኢትዮጵያውያን እየሰሙት ትልቅ ቁም ነገር የሚያገኙበት ነው'' ብለዋል።

በተጨማሪም ዜማው ችግር ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ችግርን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል የሚያስተምር እንደሆነ ተናግረዋል።

ተወካዩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህብረ ዜማው እንዲሠራ ላደረገው ድጋፍና በሙዚቃ ሥራው ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

"ቅኔ ነው አገር" በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ህብረ ዜማ የመርሃ ግብሩ ታዳሚያን እና በሙዚቃ ባለሙያዎች ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

ከህብረ ዜማው ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ሙሉ በሙሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚሠራቸው ሥራዎች እንደሚውል በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

በህብረ ዜማው ላይ ለተሳተፉ አካላት ከከተማ አስተዳደሩ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በሙዚቃ ስራው ምረቃና ርክክብ ላይ ወጣትና አንጋፋ ድምጻውያን፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች፣ የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ ታዋቂ ሰዓሊያንና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሰዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም