የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነገ ከ9 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎችን ያስመርቃል

55
አዲስ አበባ ሰኔ 28/2010 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚህ አመት ከ9 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎችን ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ ም እንደሚያስመርቅ ገለፀ። የዩኒቨርሲቲው ምክትል ሬጅስትራር አቶ መሰለ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በመደበኛ፣ በማታ፣ በርቀትና በክረምት መርሃ ግብር ያስተማራቸውን ተማሪዎችን የክብር እንግዶች በሚገኙበት ነው የሚያስመርቀው። ከተመራቂዎቹ መካከል 2 ሺህ 734 ሴቶች ናቸው። ከአጠቃላይ ተመራቂዎቹ  5 ሺህ 972 በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር የተማሩ ሲሆኑ 3 ሺህ 606 ደግሞ በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። 266ቱ በሶስተኛ ዲግሪ የሚመረቁ መሆናቸውንም ገልፀዋል። የወርቅ ሜዳሊያ ከሚሸለሙ 12 ተመራቂዎች መካከል ሰባቱ ሴቶች እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ መሰለ ውጤቱ በዩኒቨርሲቲው ለሴቶች የሚደረገውን ድጋፍና ተሳትፎ የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል። ለተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕታቸውን ያስተላለፉ ምክትል ሬጂስትራሩ ተመራቂዎች በስራ መስክ ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ ተመኝተዋል። ዘንድሮ ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ማዕረግ የማይሰጥ መሆኑን ከሬጅስትራሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም