ድንበር ተሻጋሪ ሾፌሮች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው

47

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6/2012 (ኢዜአ) ድንበር ተሻጋሪ ሾፌሮች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቅቄ ማድረግ እንዳለባቸው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

በድንበር አካበቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን ከ45 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች  በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ 272 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጉዞ ታሪክና በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው እየተረጋገጠ ይገኛል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው ከታወቁት ዘጠኝ ሰዎች መካከል ሁለቱ የጉዞ ታሪክም ሆነ የቅርብ ንክኪ የላቸውም ብለዋል።

በተለይ ቫይረሱ ወጣቶችን አያጠቃም በሚል የተሳሳተ መረጃ ምክንያት መዘናጋቶች መስተዋላቸውንም ነው የተናገሩት።

ነገር ግን በኢትዮጵያ ያለው የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ትንተና ይህን እንደማያሳይ ገልጸው፤ ቫይረሱ ከጨቅላ ሕፃናት እስከ አረጋዉያን ያሉ ዜጎች ላይ መገኘቱን አስታውሰዋል።

በተለይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ወጣቶች መሆናቸውን ነው ያብራሩት።

የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡና የሚያስወጡ በሮች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ነገር ግን በጎረቤት ሀገራት ያለው የቫይረሱ ሥርጭት መጨመሩ ጋር ታያይዞ አሁንም በነዚህ አካባቢዎች ጥብቅ ቁጥጥር ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይ በሥራ ምክንያት የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የሚያሽከረክሩ ሾፌሮች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

በድንበር አካበቢ ያለውን ቁጥጥር ይበልጥ ለማጠናከር አዳዳስ አሰራሮች እየተተገበሩ መሆኑን ጠቁመው፤ አሰራሮችን በሚመለከትም በቅርብ ለሕዝብ የተጠናቀረ መረጃ እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል።

በሕገወጥ መንገድ ድንበሮችን ተሻገረው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎችን በለይቶ ማቆያ ለማስገባት ደግሞ የማኅበረሰቡ ትብብር እጅጉን እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

በመሆኑም የአካበቢው ማኅበረሰብ ይህን ተረድቶ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም