በመቀሌ ከ1ሺህ በላይ ወጣቶች በድንጋይ ንጣፍ የመንገድ ስራ ተሰማርተዋል

91

መቐለ፣ ግንቦት 06/2012 (ኢዜአ) በመቐለ ከተማ በድንጋይ ማንጠፍ ስራ የተሰማሩ ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች ሙያውንና የስራ ባህሉን እያዳበሩ መሆናቸውን ገለጸ።

በመቀሌ በ116 ሚሊዮን ብር 14 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የድንጋይ ንጣፍ መንገድ እየተገነባ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገልጸዋል።

በመቀሌ ሓወልቲ ማህበር በሚል ስም የተደራጁ 30 ወጣቶች አስተባባሪ ወጣት  መድሀንየ  ዘወልዲ ለኢዜአ  እንደገለጸው ለአንድ ወር ያህል የድንጋይ ንጣፍ ስራ ስልጠና በመውሰድ የሙያ ባለቤት መሆናቸውን ገልጿል።

ማህበሩ 400 ሜትር ርዝመት ያለው የድንጋይ ንጣፍ ስራ ግንባታ በማከናወን ላይ ሲሆኑ በ3 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር ኮንትራት በመውሰድ ወደ ስራ መግባታቸውን አስረድቷል ።

የማህበሩ አባላት ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን አቀናጅተው በመስራት ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ  የሚያሸጋግራቸውን ትርፍ ለማግኘት እየታተሩ መሆናቸውን ከወጣት መድሃንየ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

  ''አሞራ '' የወጣቶች ድንጋይ ንጣፍ ማህበር  አባል  ወጣት ገነት ፀጋይ አሁን በተፈጠረላት የስራ እድል ሙያ ከመልመድዋ በተጨማሪ በህብረት  መስራት  ለውጤት  እንደሚያበቃ  መረዳትዋን ተናግራለች ።

''አሞራ'' የድንጋይ ንጣፍ የወጣቶች ማህበር 30 የዩኒቨርስቲ ምሩቃን ወጣቶች ያቀፈ መሆኑን የተናገረው ደግሞ የማህበሩ አስተባባሪ ወጣት በለጾም ሓዱሽ ነው።

አራት መቶ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ለመስራት ከተመደበላቸው 3 ሚልዮን ብር የተሻለ ትርፍ ለማግኘት በርትተው እየሰሩ መሆናቸውን አስረድቷል ።

 የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶች ተግባራዊ በማድረግ ስራቸው አጠናክረው መቀጠላቸውንም ወጣቱ ተናግሯል ።

በአካባቢያቸው መንገድ መሰራቱ ወደ ቤታቸው አቧራ እየገባ የታጠበ ልብስ ከማቆሸሽ  መገላገላቸው የተናገሩት ደግሞ የመንገድ ግንባታው ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ ህይወት ሙሉ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

የዓይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ገብረመድህን አማረ በበኩላቸው የመንገድ ስራው ወጣቶች የስራ እድል እንዲያገኙ ከማድረጉ ባሻገር የአካባቢውን ውበት እንዲጨምር ማድረጉን ገልፀዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የኮንስትራክሽን መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ተስፋአለም ሐዱሽ እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ ከ14 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ እየተካሄደ ነው ።

ከተማ አስተዳደሩ ለድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራው 116 ሚልዮን ብር በጀት  መመደቡና  ለአንድ ሺህ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

የኮንስትራክሽን ዘርፍና አምራች ኢንዱስትሪዎች ከኮሮና ጋር ተያይዞ ገደብ ያልተጣለባቸው በመሆኑ በሰባቱ ክፍለ ከተሞች የዩኒቨርስቲ ምሩቃን ወጣቶችን በማደራጀት ርቀታቸውን ጠብቀውና አስፈላጊውን የመከላከያ አማራጮችን በመጠቀም በድንጋይ ንጣፍ የመንገድ ግንባታ ስራ መሰማራታቸውን ኃላፊው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም