የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የጥንቃቄ እርምጃዎች መጠናከር አለባቸው- የዓለም ጤና ድርጅት

58

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ስለሚችል የጥንቃቄ እርምጃዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የዓለም ጤና ድርጅት አመለከተ።

የድርጅቱ የአስቸኳይ ጊዜ ጉዳዮች ኃላፊ ዶክተር ማይክ ርያን ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስረዱት ቫይረሱ የሚጠፋበትን ጊዜ መገመት አስቸጋሪ ነው።በቫይረሱ ላለመያዝ የሚደረገው እንቅስቃሴ ግን መቀጠል ይገባዋል።

ለበሽታው ክትባት ቢገኝለት እንኳን፤በሽታው ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመልክዋል።

''ቫይረሱ በሕዝቡ ውስጥ  የሚቆይና  ወረርሽኝ የሚያስከትል ሆኗል።ስለዚህ ቫይረሱ ቶሎ የሚወገድ አይደለም'' ብለዋል።

''ኤች አይ ቪ አልጠፋም።ነገር ግን ቫይረሱን የምንቆጣጠርበት መንገድ አለ''ያሉት ዶክተር ርያን፣የኮሮና ቫይረስ  ''የሚጠፋበትን ጊዜ ማንም ሊገምት አይችልም'' ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ ከ100 በላይ ክትባቶች በመሞከር ላይ እንደሆኑም  ኃላፊው አስታውቀዋል።

ክትባት የተገኘላቸው እንደ ኩፍኝ ዓይነት በሽታዎች ጨርሰው አለመጥፋታቸውንም በማመልከት።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው ቫይረሱን ለመቆጣጠር እንደሚቻልም ተስፋቸውን ገልጸዋል።

''በሽታውን የምንቆጣጠርበት ዕድል በእጃችን ነው።የሁላችንም ተግባር ሊሆን ይገባል።ወረርሽኙን ለመግታት ድርሻችን መወጣት ይገባናል'' ብለዋል።

አገሮች ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የወሰዷቸው  እርምጃዎች  መጠናከር እንጂ፤መላላት እንደሌለባቸውም ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

ኮቪድ 19 በዓለም  ወደ 300ሺህ ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፈና ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎችን ደግሞ እንደያዘ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም