የደቡብ ክልል ሕዝብ ኮቪድ-19 ወረረሽኝን መከላከል ላይ መዘናጋት ይታይበታል-የክልሉ ጤና ቢሮ

65

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4/2012(ኢዜአ) የደቡብ ክልል ሕዝብ የኮቪድ-19 ወረረሽኝ በመከላከል ረገድ የሚያሳየው መዘናጋት እንዳሳሰበው የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ እስከ ግንቦት 1 ቀን 2012 ድረስ ስድስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተዋል።

ኅብረተሰቡ ወረርሽኙን ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት ለሥጋት ይዳርጋል ሲሉ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ ተናግረዋል።  

በቫይረሱ ከተጠቁ ግለሰቦች መካከል አንዷ ከሞያሌ ወደ ክልሉ የገባች ሲሆን አንደኛው ደግሞ ለተጓዳኝ ሕክምና ወደ ሆስፒታል በመጣበት ወቅት በምርመራ በቫይረሱ እንደተረጋገጠ ይናገራሉ።

ይህም በክልሉ ውስጥ የተዋህሱ መኖሩንና መዛመቱን የሚያረጋገጥ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ኅብረተሰቡ ግን አሁን ላይ ያለው እንቅስቃሴ ለቫይረሱ መዛመት የሚያጋልጥ ነው ይላሉ። ሁኔታውንም ''አሳሳቢ'' ብለውታል።

ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ካላደረገ በሣይንሳዊ ጥናት መሠረት ከ12 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በወረርሽኙ ይጠቃል የሚል ሥጋት እንዳለ ኃላፊው ገልጸዋል።

መረጃው ሣይንሳዊ መሠረት ያለውና እንደ አገር ካለው ሥጋት አንጻር መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥንቃቄው ከተደረገ ግን ሥጋቱን መሻገር እንደሚቻል አመልክተዋል።

ኅብረተሰቡን ከማስተማር አንጻር በሚዲያ፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶችና ታዋቂ ሰዎችን በመጠቀም ጥረት ቢደረግም የተፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ አብራርተዋል።

ኅብረተሰቡም የሥጋቱን ክብደት በማጤን "ቆም ብሎ ማሰብ አለበት" ብለዋል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞም ኅብረተሰቡን ከማስተማር ባለፈ ሕግ ማስከበር ሌላው አማራጭ እንደሆነ አቶ አቅናው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም