ጅቡቲ ዓለም አቀፍ ነጻ የንግድ ቀጠና ከፈተች

62
አዲስ አበባ ሰኔ 28/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጅቡቲ መንግስት ባስገነባው ዓለም አቀፍ ነጻ የንግድ ቀጠና የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኙ። ከሀገሪቷ ወደብ ጋር ተገናኝቶ በሙከራ ደረጃ ዛሬ የተመረቀው ፕሮጀክቱ 240 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በአፍሪካ ትልቁ ነፃ የንግድ ቀጠና እንደሆነም ተነግሮለታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በቅርቡ ጅቡቲን ጨምሮ በጎሮቤት አገራት ባደረጉት ጉብኝት ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ውህደት መፍጠር ላይ ትኩረት አድርገው መወያየታቸው ይታወሳል። በዛሬው ዕለት በጂቡቲ የተመረቀው ነጻ የንግድ ቀጠናም የዚሁ አካል በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃው ላይ መገኘታቸው ፋይዳው የላቀ መሆኑ ተገልጿል። ከአሁን ጀምሮ አስከ መጪዎቹ አስር ዓመታት ድረስ ደረጃ በደረጃ ግንባታው የሚቀጥለው የንግድ ቀጠና ፕሮጀክቱ በጠቅላላው 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚፈጅና አጠቃላይ ስፋቱም ከ 4 ሺህ ሄክታር በላይ እንደሚሆን ተገልጿል። ነፃ የንግድ ቀጠናው የውጭ ባለኃብቶቸ የሚፈልጓቸውን ዓይነት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ለመትከል የሚያስችል ሲሆን፤ ዓላማውም የጅቡቲን ምጣኔ ኃብት ምንጭ ማስፋት፣ የውጭ ምንዛሪ አቅምን ማሳደግና ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መሆኑም ተመልከቷል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገጻቸው እንደገለፁት ኢትዮጵያ የወደብ አጠቃቀምን በመተመለከተ ለውጤታማ የሎጅስቲክ ሰንሰለት፣ የሎጂስቲክ ዋጋና ጊዜን ለመቀነስ ቅድሚያ ትሰጣለች። የጅቡቲ ወደብ የኢትዮጵያ አስመጪና ላኪዎች ጥቅም ለማስከበር በሚያስችል መልኩ ኢትዮጵያ የመፍትሄ ኃሳብ እንደምታቀርብም ገልጸዋል። ጎን ለጎንም ኢትዮጵያና ጅቡቲ የተጣጠመ የወደብ ሥራ ሠዓት ማመቻቸት፣ ተወዳዳሪ የወደብ ታሪፍ፣ አንድ ነጻ ማድረጊያ ሰነድና ስትራቴጂክ ሰርቪስ የሚያካሄድ ቢሮ ለመገንባት አገሪቷ እንደሚትሻ ነው የገለጹት። በተጓዳኝም ኢትዮጵያ ወደብን በተመለከተ በጋራ ማልማትና የተሻሻለ የመንገድ መሰረተ ልማት በተለይም በጋዳፊና በጂቡቲ ለማስጀመር  ፍላጎቷ መሆኑን ጠቁመዋል። የጅቡቲ መንግስት ነፃ የንግድ ቀጠናውን የሚያስተዳድረው ከሶስት የተለያዩ የቻይና ኩባንያዎች ጋር በጋራ መሆኑም ተገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም