በደቡብ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚከናወኑ ዝግጁነትና ምላሽ ሥራዎች መጠናከር አለባቸው- የጤና ሚኒስቴር

47

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4/2012 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ክልሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያከናውናቸው ዝግጁነትና ምላሽ ሥራዎች እንዲጠናከሩ አሳስበዋል።

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እገዛ እንደሚያስፈልግ ኃላፊዎች ተናግረዋል።

በሚኒስትር ዴኤታው የተመራ ቡድን በክልሉ የሥራ ጉብኝት አድርጓል።

የደቡብ ክልል የኮቪድ 19 ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመከላከል የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ያስፈልገዋል ብለዋል።

በአገሪቱ ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል።

ግብረ ኃይሉ ከክልል እስከ ወረዳ መከላከል ተዋቅሮ እስካሁንም ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች ዳሰሳ ቅኝት የተደረገ ሲሆን፣ 155 ስልኮች መለየታቸውንና ነጻ የጥቆማ ስልክ መሥመር 486 መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

እንዲሁም በሐዋሳ የምርመራ ላብራቶሪ መቋቋሙንና 282 ናሙናዎች መመርመራቸውን አስታውቀዋል።

ያም ሆኖ ግን ከጥራትና መልክዓ ምድራዊ ተደራሽነት አኳያ ክፍተቶች እንዳሉም አቶ እንዳሻው አስረድተዋል።

እስካሁንም በክልሉ 19 የህክምናና ማስታመሚያ ማዕከላትና 34 የለይቶ ማቆያ ማዕከላት መቋቋማቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ካሉት 3 ሺህ 218 የህክምና አልጋዎች ውስጥ 440 ለኮሮና ህሙማን ብቻ መዘጋጀታቸውን ገልጸው፣183 የኦክስጂን ሲሊንደሮችና 24 የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎችም መዘጋጀታቸውን ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል።

በየዞኖቹ ያለው አፈጻጸም ተመዝኖ በሰው ኃይል፣ በህክምና ማዕከላት ዝግጁነት፣ በህክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ደረጃ ሲመዘኑ በአማካይ ጥራታቸው ከ20 በመቶ እንደማይበልጥ ጠቅሰዋል።

ክልሉ ከሐዋሳ በተጨማሪ በዓርባ ምንጭ፣ በሶዶና ሐዲያ የላቦራቶሪ ምርመራ ለማካሄድ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚሻ ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል።  

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃለፊ አቶ አቅናው ካውዛ በበኩላቸው የጤና ባለሙያዎች ተነሳሽነት አበረታች መሆኑንና ከክልሉ አቅም በላይ የሆኑ የህክምና ግብዓቶች ግን ሊሟሉ ይገባል ብለዋል።

በሚኒስትር ዴኤታው የተመራው ቡድን በሲዳማ፣ በሃላባና ስልጤ ዞኖች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚካሄዱትን የመከላከል ሥራዎች ጎብኝቷል። ከክልሉና ከዞኖች ሥራ ኃላፊዎች ጋርም ተወያይቷል።

በሐዋሳ ማዕከል ያለው ተሞክሮም አድንቀዋል።

የባለሙያዎች የራስ መጠበቂያ ቁሳቁስ አጥረት፣ጥቅማ ጥቅም አለመጠበቅና ከመሠረታዊ አገልግሎት አንጻር ያሉ ክፍተቶችን ለማሟላት ጥረት እንደሚደረግ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የክልሉ የምርመራ አቅሙን ማሳደግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የወቅቱ የብሔራዊ የኮቪድ 19 ዝግጁነትና ምላሽ ዋና አስተባባሪ አቶ አስቻለው አባይነህ በበኩላቸው የማህበረሰብ አቀፍ ዳሰሳ ሥራዎች እንዲጠናከሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም