የሻምቡ ባኮ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት በቃ

72

ነቀምቴ፣ ግንቦት 04/2012 (ኢዜአ) የሻምቡ ባኮ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ገለፀ፡፡

የባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሣምሶን ወንድሙ እንደገለፁት ባለፉት አራት ዓመታት በግንባታ ላይ ቆይቶ በአሁኑ ወቅት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የአስፋልት መንገድ 993 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።

60 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአስፋልት መንገድ በክልሉ የሚገኙትን የሆሮ ጉዱሩ ወለጋንና የምዕራብ ሸዋን ዞኖች በአቋራጭ የሚያገናኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንገዱ በወረዳ ከተማ 19 ሜትር በገጠር ደግሞ 10 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን የበጀት ምንጩ ደግሞ የዓረብ ባንክ፣ ኦፔክና የኢትዮጵያ መንግሥት ናቸው።

የመንገዱ መገንባት በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች፣ አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አቶ ሣምሶን ገልፀዋል።

በተጨማሪም መንገዱ የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ምርቱን በፍጥነትና በቅርበት ወደ ገበያ እንዲያቀርብ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

 የሻምቡ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የመንገዱ ግንባታ ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት መሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጠቀሜታው በገንዘብ የማይተመን መሆኑን ገልፀዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ደሣለኝ ተረፈ በሰጡት አስተያየት አርሶ አደሩ የምርት ማሣደጊያ ግብዓቶችን በጊዜ እንዲደርሱለትና የግብርና ውጤቶቹን ወደ ገበያ በመውሰድ በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም እናቶችንና ሕፃናትን ወደ ህክምና ተቋማት ለመውሰድና አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ቦጀር በየነ በበኩላቸው መንገዱ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ለዘመናት መልስ ሳያገኝ የቆየውን የዞኑ ሕዝብ ጥያቄ የመለሰ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም