ኢትዮጵያ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝና 60 ቀናት ዓበይት ሁነቶች

56

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) የተያዘው የመጀመሪያ ሰው ከተገኘ ዛሬ ሁለት ወር ሆኖታል።

ታኅሣሥ 21 ቀን 2012 የኮሮና ቫይረስ(ኮቪድ-19) በቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ዉሃን ከተማ መከሰቱ የተሰማበት ቀን ነበር።

ቫይረሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተስፋፍቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ በቫይረሱ ተጠቅተዋል።

በኢትዮጵያም የቫይረሱ የመጀመሪያ ተጠቂ መጋቢት 4 ቀን 2012 ተገኘ።ይህም ከቡርኪናፋሶ የመጡት የ48 ዓመት ጃፓናዊ ዜጋ ቫይረሱን በአገሪቱ ካስመዘገቡ ዛሬ ሁለት ወር ሞልቶታል።

በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቃው የመጀመሪያው ሰው ከታወቁ በኋላ ንክኪ በነበራቸው ሰዎች ላይ ክትትል ተደርጓል።

በዚሁ መሠረት መጋቢት 6 ቀን  የ44 ና የ47 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ጃፓናውያን እንዲሁም የ42 ዓመት ኢትዮጵያዊ ተገኝተዋል።

ቀኑ በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) የተያዘው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የተገኘበት ሲሆን፣ ግለሰቡም ከመጀሪያው ጃፓናዊ ጋር ንክኪ ያለው የ42 ዓመት ዕድሜ ያለው ኢትዮጵያዊ ነው።

ኢትዮጵያ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል መጋቢት 13  ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ከውጭ የሚገቡ መንገደኞች ለ14 ቀናት በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እንዲቀመጡ ወስናለች።

መጋቢት 14 በኮሮና ቫይረስ የተያዙት ሁለት ጃፓናውያን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የጤና ሚኒስቴር ማሳወቁ የሚታወስ ነው።

መጋቢት 18 ከአዲስ አበባ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ግለሰብ የተገኘበት ዕለት ነው።

ግለሰቡ የ61 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፣ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ ባይኖራቸውም ከአንድ የውጭ ዜጋ ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ተገልጿል።

መጋቢት 19 ከቫይረሱ ሙሉ ለመሉ ያገገመ የመጀመሪያው ሰው መገኘቱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተገለጸበት ዕለት ነበር።

መጋቢት 21 በቫይረስ ተይዘዋል ተብለው ከተለዩት መካከል የ24 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ከቫይረሱ ነጻ መሆኗ ተገልጿል።

መጋቢት 22 ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተጨማሪ የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩትና ሰበታ በሚገኘው የብሔራዊ እንስሳት ጤና ምርምርና ጥናት ማዕከል(ናዲክ) የቫይረሱን ምርመራ መጀመራቸው ይፋ የተደረገበት ዕለት ነው።

መጋቢት 27 ኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮሮና ቫይረስ ህይወቱ ያለፈውን ሰው ያሳወቀችበት ቀን ነው።

ህይወታቸው ያለፈው የ60 ዓመት ታማሚ ሴት፣ ለስድስት ቀናይ በጽኑ ሕሙማን የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተዋል።

በዚያው ቀን በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ሁለተኛ ሰው የሞተ ሲሆን፣ የ56 ዓመቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ  ለአራት ቀናት በጽኑ ህሙማን ክፍል ታክመዋል።

ሚያዚያ 2 በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ሶስተኛው ሟች የተመዘገበበት ዕለት ነው።የ65ቱ ዓመቷ ሴት የዱከም ከተማ ነዋሪ በጽኑ ሕክምና ክፍል ሲረዱ ቆይተዋል።

ሚያዚያ 14 ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀን ከአንድ ሺህ በላይ የላቦራቶሪ ምርመራ ያደረገችበት ነው።

በዕለቱ ኢትዮጵያ 1 ሺህ 73 ምርመራ ተደርጎ ሁለት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተገልጿል።

ሚያዝያ 24 ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀን ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች ተመርምረዋል።

ከተመረመሩት መካከል በቫይረሱ የተያዘ ሰው እንዳልተገኘም ተዘግቧል።

ሚያዚያ 27 የአራተኛው ሰው ሞት ተመዝግቧል።የ75 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሴት በተጓዳኝ ሕመም ሆስፒታል ተኝተው ሲከታተሉት የነበረው ሕክምና በበሽታው ተጠርጥረው ናሙና ተወሰደ በኋላ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከመረጋገጡ በፊት ሕይወታቸው አልፏል።

ሚያዚያ 28 በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 17 የተመዘገበበት ቀን ሆኗል።

ሚያዚያ 29 ደግሞ 29 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተገለጸበት ዕለት ሆኖ ተመዝግቧል።

ግንቦት 1 በቫይረሱ የተያዙ 16 ሰዎች ምዝገባ የተከናወነበት ነው።ዕለቱ  በቫይረሱ  አምስተኛው ግለሰብ  ሞተዋል። ሟቹ  የ65 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ወንድ ነበሩ።

ግንቦት 2  ደግሞ 29 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተመዘገቡበት ቀን ሆኖ አልፏል።

ግንቦት 3 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 11 ነበር።

ካለፉት ስድስት ተከታታይ ቀናት አምስቱ ባለ ሁለት አኅዝ ሰዎች ተመዝግበዋል። በአንድ ሳምንት 104 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን 36 ሺህ 624 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቷር ምርመራ ተደርጎ 250 ሰዎች  በቫይረሱ ተይዘዋል።

ከዚህም ውስጥ 189ኙ ወንዶች፤ 61ቱ ሴቶች ናቸው።

በቫይረሱ ከተያዙት 121ዱ የውጭ የጉዞ ታሪክ አላቸው። 81ዱ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ የላቸውም። 25ቱ  ደግሞ የውጭ የጉዞ ታሪክም ሆነ በበሽታው ከተያያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የላቸውም።

ስድስቱ የውጭ የጉዞ ታሪክም በበሽታው ከተያያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው ሲሆኑ፣13ቱ ሰዎች በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ያላቸው ግንኙነት በመጣራት ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

አራት ሰዎች ደግሞ የሥራ ባህሪያቸው ተጋላጭ ያደረጋቸው ናቸው።

ምርመራው ከዘጠኝ ወር ጨቅላ ህጻን እስከ 85 አዛውንት ቫይረሱ ተይዘዋል።

በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች ሁለቱ በቤት ለቤት አሰሳ እንደተገኙ ተመልክቷል።

በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 228ቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ 22ቱ የውጭ ዜጎች ናቸው።

የውጭ ዜጎች ከ13 አገሮች የተውጣጡ ሲሆን፣ አምስት እንግሊዛውያን፣አምስት ቻይናውያን፣አምስት ኤርትራውያንና አራት ጃፓናውያን በቫይረሱ ተይዘዋል።

የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ሞሪሺየስ፣ ሊቢያ፣ ሕንድ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ስዊድንና የሶማሊያ ዜጎች በቫይረሱ መያዛቸው ምርመራዎቹ ያሳያሉ።

ከ28ቱ የውጭ አገር ዜጎች አራቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

በቫይረሱ የሞቱት ግለሰቦች ዕድሜያቸው ከ56 እስከ 75 ዕድሜ ክልል ነው።

በመጀመሪያው ወር 69 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ፣ በሁለተኛው ወር ደግሞ 181 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።

የሶማሌ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች በቫይረሱ የተያዙ ግለሰቦች አስመዝግበዋል።

በአጠቃላይ አስከ ግንቦት 3/2012 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙት 250 ሰዎች ውስጥ 138 ሰዎች በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ሲሆን፣105 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል።

በዓለም እስካሁን 286 ሺህ 355 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሞተዋል። ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ከቫይረሱ ማገገማቸውን የአሜሪካው ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም