በአማራ ክልል የ2ሺህ 774 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታና ጥገና ስራ ተከናወነ

98

ባህርዳር፣ ግንቦት 4/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከመከላከል ጎን ለጎን 2 ሺህ 774 ኪሎ ሜትር የአዲስ መንገዶች ግንባታና የነባር መንገዶች ጥገና ስራ መከናወኑን የክልሉ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ገለፀ።

የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ጌትነት ዘውዱ ለኢዜአ እንደገለጹት በመንገድ ስራ ፕሮጀክቶቹ ሰራተኞች ለኮሮና ቫይረስ አጋላጭ ከሆኑ ንክኪዎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ ግንዛቤ ተፈጥሯል።

እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያሳኒታየዘርና የመታጠቢያ ሳሙና በማቅረብ የፕሮጀክቶቹ ስራ ሙሉ በሙሉ እንዳይቆም ተደርጓል።

በተደረገው እንቅስቃሴም በአዲስ ከተገነቡት መንገዶች መካከል 162 ኪሎ ሜትር ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ ግንባታ ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል።

እንዲሁም 2 ሺህ 612 ኪሎ ሜትር ከዚህ ቀደም የተገነቡና በአገልግሎት ብዛት ምክንያት ለብልሽት የተዳረጉ ነባር መንገዶች መጠገናቸውን ገልፀዋል።

የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎቹ የተከናወኑት በክልሉ በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች በበጀት ዓመቱ ለመገንባትና ለመጠገን በዕቅድ ከተያዘው 3 ሺህ 796 ኪሎ ሜትር መንገድ ውስጥ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

እስከ አሁን ለተከናወኑ የግንባታና የጥገና ስራዎች ከክልሉ መንግስትና ከፌዴራል መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት 650 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጭ ተደርጓል።

ከወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ የአቅርቦትና የበጀት እጥረት ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተዳምረው ስራው  በሚጠበቀው ልክ ማከናወን እንዳልተቻለ አቶ ጌትነት ተናግረዋል።

የመንገድ መሰረተ ልማቶቹ መስፋፋት ወረዳን ከወረዳና ቀበሌን ከቀበሌ በማገናኘት አርሶ አደሩ ክረምት ከበጋ የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችለዋል።

ይህም ያመረተውን ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግና የግብርና ግብዓት በወቅቱ ለማግኘት ያግዘዋል።

በቀጣይም የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ ከመከላከል ጎን ለጎን የቀሪ ፕሮጀክቶች ግንባታና ጥገና ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አብራርተዋል።

በአዊ ዞን እየተገነባ ያለው የአይማ ገንገን የ48 ኪሎ ሜትር  የመንገድ ስራ  ፕሮጀክት  ችግራቸውን እንዳቃለለው የገለጹት ደግሞ በአዊ ዞን ጃዊ ወረዳ የባምብሉክ ቀበሌ አርሶ አደር እንየው አለኽኝ ናቸው።

የመንገዱን መገንባት ተከትሎ አይማ በሚባል ትልቅ ወንዝ ላይ 40 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይ መገንባቱ የአካባቢውን ነዋሪ በክረምት ወቅት በውሃ ሙላት ከመበላት ታድጎታል ብለዋል።

የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃን ፀጋዬ በበኩላቸው መንገዱ ጃዊን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን አለፋ ወረዳ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ያመረቱትን ምርት በቀላሉ ለገበያ እንዲያቀርቡ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመትም ከ3 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር በላይ የአዲስ መንገዶች ግንባታና ነባር መንገዶች ጥገና ስራ መከናወኑን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም