አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ ጋር ተወያዩ

88


ግንቦት 3/2012(ኢዜአ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች በውይይታቸው የሁለቱን አገራት ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ማጠናከር፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን በትብብር ለመግታት፣ሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በደማቅ ሁኔታ ማክበር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች እና ተያያዥ ገዳዮች ዙሪያ ትኩረት አድርገው መክረዋል።

አቶ ገዱ ቻይና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተከተለችው ውጤታማ ስትራቴጂ ለቀረው ዓለምም መልካም ተሞክሮ በመሆኑ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። የኮሮና ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ዘመቻ የሁሉም አካላት ትብብር ተጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።

የቻይና የህክምና ቡድን አባላት በቅርቡ በኢትዮጵያ በመገኘት ወረርሽኙን ለመግታት ላደረጉት ድጋፍ እና የክህሎት ሽግግርም አቶ ገዱ ምስጋና አቅርበዋል።

ኮቪድ 19 በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ የከፋ ጉዳት አንዳያደርስ ቻይና እያደረገች ላለው የመከላከያ ቁሳቁስ እና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አቶ ገዱ አመስግነው፤ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

አቶ ገዱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ እና የኢትዮጵያን አቋም በተመለከተም ለዋንግ ዪ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ አሁንም የሶስትዮሽ ድርድሩ ቀድሞ በተቀመጡ መርሆች ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍተሄ ሊሰጥ በሚችል መልኩ እንዲቀጥል ቢደረግ ፍላጎቷ መሆኑንም አቶ ገዱ በውይይቱ አንስተዋል።

ሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በደማቅ ሁኔታ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ይህም የሁለቱን አገሮች ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የጎላ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት የዓለም ጤና ድርጅት የሚሰጠውን ምክረ ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ስራ ሁሉም አካላት ሊደግፈው ይገባልም ብለዋል።

ወረርሽኙ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ቻይና ያላትን ልምድና ተሞክሮ ማካፈሏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልጸዋል።

ቻይና ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ኢኮኖሚ እድገት የምታደርገውን ድጋፍ በዚህ ወሳኝ ወቅትም ከምንጊዜውም በተሻለ አጠናክራ ትቀጥላለችም ነው ያሉት ዋንግ ዪ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ውሃ ሙሌትን በተመለከተ ሶስቱ አገሮች በመርህ ላይ የተመሰረተ ውይይት በማድረግ መፍትሄ ማፈላለግ አለባቸው ብለው እንደሚያምኑም ዋንግ ዪ ገልጸዋል።

ቻይና ሶስቱ አገሮች ተቀራርበው ልዩነታቸውን እንዲፈቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለችም ብለዋል።

የቻይናና የኢትዮጵያ ግንኙነት በአፍሪካ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው ያሉት ዋንግ ዪ፤ ሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በደማቅ ሁኔታ ለማክበር እያደረጉ ያለው ዝግጅት ለዚሁ ማሳያ ነውም ብለዋል።

ሁለቱ አገሮች በመደበኛነት የሚያደርጓቸው የሁለትሽና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ከምንጊዜውም በተሻለ ተጠናክረው በመቀጠላቸው ቻይና በእጀጉ ደስተኛ መሆኗንም ዋንግ ዪ በውይይታቸው ማንሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም