ኮቪድ-19 እና የኢትዮጵያ የውሃ እጥረት

132

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ አለምን እግር ከወርች በመያዝ እያስጨነቀ በሚገኝበት በዚህ ወቅት እንደ ውሃ ያሉ የመሰረታዊ ፍላጎት አገልግሎት አቅርቦት ዝቅተኛ የሆነባቸው አገሮች የማያባራ መከራ ውስጥ እየገቡ ነው።

ኢትዮጵያን የመሰሉ የአፍሪካ አገሮች የውሃ እጥረት፣ መሰረታዊ የጤና አጠባበቅ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ችግር በእጅጉ የተጋረጠባቸው መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።

በሰዎች ላይ ከሚከሰቱት ተላላፊ በሽታዎች ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚጠጉት ምንጫቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት አለመኖርና ዝቅተኛ የንፅህናና የጤና አጠባበቅ ችግር እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያ 42 በመቶ የሚጠጉ ሰዎች ንፁህ ውሃ የሚያገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል ደግሞ 11 በመቶ የሚጠጉት ብቻ በቂ የሆነ የንፅህና መጠበቂያ እንዳላቸው 'ዋተር ኦርግ' ተቋም ያደረገው ጥናት ያሳያል።

በገጠራማ የአገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ይህ ተደራሽነት በእጅጉ ዝቅ ያለ ነው፤ በዚህ የተነሳ በነዋሪዎቹና በቀንድ ከብቶቻቸው ላይ ተደጋጋሚ የጤና ችግር መከሰቱ የተለመደ ሆኗል።

ከአገሪቱ ህዝብ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው የንፁህ መጠጥ ውሃ እንደማያገኝ ሌላ ጥናት ያሳያል። ከአገሪቱ ህዝብ 32 ሚሊዮን የሚጠጋው ለእለታዊ ፍጆታ ጤንነቱ ያልተረጋገጠ ውሃ የሚጠቀም መሆኑን 'ጆይንት ሞኒተሪንግ ፕሮግራም' የተባለ አለም አቀፍ የውሃ፣ የጤናና የንፅህና አጠባበቅና መረጃ አጠናቃሪ ተቋም ጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪ ''28 በመቶ የሚጠጋው ህዝብ በጤና ላይ ጉዳት የማያደርስ ውሃ የሚያገኝ ቢሆንም  ውሃውን ለመቅዳት ግን ከ30 ደቂቃ በላይ መጓዝ ያለባቸው ናቸው'' ይለናል። በኢትዮጵያ ከ62 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የማያገኝ ነው።

ኢትዮጵያ ብቻዋን የአለምን 7 ነጥብ 5 በመቶ የውሃ ቀውስ የተጋፈጠች አገር መሆኗን ጥናቱ ያመላክታል።

መሰረታዊ እጅ የመታጠብ ተግባር ሳርስንና ኮቪድ-19 የመሰሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል ዋነኛ መፍትሄ ቢሆንም የውሃ እጥረት እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ዋነኛ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።

ጆይንት ሞኒተሪነግ ፕሮግራም ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ 41 በመቶ የሚጠጉ አባወራዎች የእጅ መታጠቢያ ቁስ የላቸውም።

51 በመቶ የሚጠጉት አባወራዎች ደግሞ የመታጠቢያ ቁሱ ቢኖራቸውም የንፁህ ውሃ እና የሳሙና አቅርቦትን አያገኙም። የተቀሩት 8 በመቶ አባወራዎች ንፁህ ውሃና ሳሙናን ያገኛሉ ይላል መረጃው።

ይህም የአገሪቱን የጤና እና የንፅህና አጠባበቅ እንቅስቃሴ በመገደብ በርካታ ህዝቦችን እየጎዳ ይገኛል። ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች በርካታ ወንዞች ያሏት ቢሆንም  ከተፈጥሮ ሃብቷ 3 ከመቶ የሚጠጋውን ብቻ ትጠቀምበታለች።

በገጠር የአገሪቱ አካባቢዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚሸፈነው ከጉድጓድ በሚወጣ ውሃ ነው። ከዚህ ባለፈ ምንም አይነት የውሃ አቅርቦት የማያገኙ ነዋሪዎች ደግሞ ውሃ የሚያገኙት ከወንዝ በመቅዳት፣ ደህንታቸው ካልተጠበቁ ምንጮችና በእጅ ከተቆፈሩ የውሃ  ጉድጓዶች ነው።

ችግሩን የበለጠ አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ የአገሪቱ በርካታ ወንዞች እጅግ የተበከሉና ለመጠጥ ፣ለእጅ መታጠቢያና ለቤት ውስጥ አገልግሎት ጥቅም ላይ የማይውሉ መሆናቸው ነው።

በኢትዮጵያ ለወንዞችና ለከርሰ ምድር ውሃ መበከል ዋነኛው ምክንያት የህዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመር፣ ቁጥጥር አልባ የከተሜነት መስፋፋትና ደካማ የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት ናቸው።

''በአዲስ አበባ የሚገኙ ወንዞች ከከተማዋ የሚወጡ ሁሉም አይነት ቆሻሻዎች ማረገፊያ ናቸው'' ይለናል ጥናቱን የሰራው ተቋም።

ከወንዞቹ አብዛኛዎቹ መክሰማቸውንና የተቀሩትም ቢሆኑ የተበከሉ በመሆናቸው ውሃው ለመጠጥ አይደለም ለመስኖ ልማትና ለከብቶች አደገኛ እንደሆነ በርካታ ጥናቶች መጠቆማቸውን ዘገባው ያሳያል።

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ድርቅ የምትጠቃ በመሆኑ ውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ዋነኛ መሰረታዊ ፍላጎት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

ከዚህ በተጨማሪ ኮቪድ-19ና መሰል ወረረሽኞችን ለመከላከል ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ምትክ የሌለው መሳሪያ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም