ግብጽ የህዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ ለተመድ ላቀረበችው ቅሬታ ምላሽ የሚሆን ሰነድ ተዘጋጀ

55

አዲስ አበባ  ግንቦት  3/2012  (ኢዜአ) ግብጽ የህዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት ላቀረበችው ቅሬታ ምላሽ የሚሰጥ ሰነድ መዘጋጀቱን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አሁን ላይ ያለበት ደረጃና ከታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ለሚነሱ ጥያቄዎች እየተሰጠ ያለውን ምላሽ አስመልክቶ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ 21 በመቶ የሚሆኑት የአገሪቷ ህዝቦች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ።

ለዚህ ደግሞ ተለዋዋጭ የአየር ሁኔታና ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ጉልህ ድርሻ ይይዛሉ።

ኢትዮጵያ ''የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ'' የሚል ስያሜን ብታገኝም አብዛኞቹ ወንዞቿ ድንበር ተሻጋሪ ከመሆናቸው ባለፈ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ላይ እየዋሉ አይደለም።

እንደ ዶክተር ኢንጀነር ስለሺ ገለጻ፤ ለአንድ አገር ዘላቂ ልማት የኤሌክትሪክ ሃይል መሰረተ ልማትን ማሟላት ወሳኝ በመሆኑ ኢትዮጵያም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የጀመረችው ይህን ታሳቢ አድርጋ ነው።

ኢትዮየያ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መመሪያን የምታከብር በመሆኗ በዚሁ መሰረት የህዳሴው ግድብ ግንባታ መጀመሩን አስረድተዋል።

ሰሞኑን ግብጽ የህዳሴ ግድቡ ውሃ ሙሌትን አስመልክቶ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ላቀረበችው አቤቱታ ምላሽ የሚሆን ሰነድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ከግድቡ ግንባታ ጀምሮ በቂ ገለጻና ማብራሪያ እየተደረገላቸው መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።።

በታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች እየተነሳ ያለው ጥያቄ ተገቢ የአገሪቷን የመልማት መብት የሚጋፋ ብሎም ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው መሆኑን በማንሳት።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ በባለሙያዎች፣ በሚኒስትሮችና በመሪዎች ደረጃ ከታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ጋር የተለያዩ ውይይቶችና ድርድቶችን ብታደርግም ድርድሩ መቋጫ እንዳልተገኘለት ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ገልጸዋል።

''ይህ ደግሞ አገሪቷ ጥቅሟን አሳለፋ እንደማትሰጥና የሚያሳይ ነው'' ብለዋል

ውይይቱን የህዳሴ ግድቡ ተደራዳሪዎችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እየተሳተፉበት ሲሆን በማጠቃለያው ተጨማሪ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም