የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ወደ ማምረት ሊሸጋገር ነው

140

ባህር ዳር (ኢዜአ) ግንቦት 03/2012. የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ለግብርናና ኢንዱስትሪ የሚሆኑ መሳሪያዎች ለማምረት የሚያስችል ዝግጅት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።
በባህርዳር ከተማ የሚገኘው የመሳሪያዎች  ማምረቻ በክልሉ ካቢኔ አባላት ተጎብኝቷል።

የኢንተርፕራይዙ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ጌራ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት እንተርፕራይዙ በአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የተለያዩ ማሽኖችን ለማምረት ዝግጅት ተደርጓል።

ኢንተርፕራይዙ በኮምቦልቻ የግብርና ማምረቻ ማሽነሪዎችን በባህርዳር ደግሞ የኢንዱስትሪ፣ የብረት ማቅለጫና የመብራት ትራንስፎርመር መስራትና የጥገና ስራዎችን ያከናውናል።

የትራንስፎርመር ጥገና ቀደም ብሎ መጀመሩን ጠቅሰው የማሽነሪ ማምረት ስራውን ለማስጀመር የማምረቻ መሳሪያዎች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

ለኢንዱስትሪዎቹ የሚሆን የሰው ሃይል ቀደም ብሎ መሰልጠን መጀመሩን የገለፁት አቶ ዳንኤል በቅርቡ የማሽን ተከላ ስራውን በማጠናቀቅ በመጭው ሁለት ወራት ወደ ማምረት ይገባል።

በኢንተርፕራይዙም ለጊዜው አነስተኛና መካከለኛ የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የኮንስትራክን ማሽነሪዎችን ማምረትና ታላላቅ ማሽነሪዎችን ደግሞ የመገጣጠም ስራ ይከናወናል።

የማምረት ስራውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ከ739 ኢንተርፕይዞች ጋር ትስስር ተፈጥሮ እንደሚሰራ ጠቅሰው ለጊዜው የተሻለ አቅም ያላቸውን 88 ኢንተርፕራይዞች በመምረጥ ለትስስር መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።

የአማራ ክልል የመንግስት ልማት ድርጅቶች ስራ አስኪያጅ አቶ መጋቢያው ጣሰው በበኩላቸው በክልሉ መንግስት የሚደገፉ 12 ድርጅቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።

እነዚህ ድርጅቶች ከሰባት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቅሰው ለ8 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን አመልክተዋል።

የልማት ድርጅቶቹ የክልልን አቅም መሰረት ያደረጉ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት የአቅማቸውን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማድፍሮ በበኩላቸው የክልሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከኢንዱስትሪው ጋር ያለው ትስስር ደካማ ነው ብለዋል ።

በተለይም ግብርናው አሁንም ድረስ የአርሶ አደሩን የጉልበት ድካም የሚቀንሱና ምርታማነቱን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት እጥረት በሰፊ መሆሩን ተናግረዋል።

የግብርና ምርቶቹም እሴት ተጨምሮባቸውና ዋጋቸው ከፍ ብሎ ለሃገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ሃገራት ገበያ እየቀረበ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

በመሆኑም ክልሉ ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ቴክኖሎጂ ማስፋፋትና የተጠቃሚውን ቁጥር ማሳደግ የግድ ይላል።

ለዚህም የአማራ ብረታብረት የሚስተዋለውን የቴክኖሎጂ አቅርቦት እጥረቱን በመፍታት ግብርናው በማዘመን እንዲያግዝ ለማድረግ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

በመንግስትም ሆነ በግል የኢንቨስትመንት ማስፋፋት ፈተና የሆነውን የብድርና የመብራት ሃይል አቅርቦት እጥረት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በጉብኝቱ የተሳተፉ የክልሉ ካቢኔ አበላት በተከላ ላይ የሚገኘው የኢንዱስትሪ መሳሪያዎች  ማምረቻ ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም