ከአፕል ችግኝ ሽያጭ በዓመት እስከ 120 ሺህ ብር ገቢ እያገኘን ነው… የምስራቅ ጎጃም ዞን ወጣቶች

88
ደብረ ማርቆ ሚያዚያ 30/2010 በማህበር ተደራጅተው በአፕል ችግኝ ማፍላትና መሸጥ ስራ የተሰማሩ የምስራቅ ጎጃም ዞን ወጣቶች በዓመት እስከ 120 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለፁ። በዞኑ የአፕል ልማትን ለማስፋፋት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡ የስናን ወረዳ  ነዋሪ ወጣት ፈንቴ አገኝ  እንደገለፀው ሦስት ሆነው በመደራጀት  የአፕል ችግኝ በማፍላት ለገበያ እያቀረቡ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የእርሻ መሬት ስላልነበረው በቤተሰብ ድጎማ ይኖር እንደነበር አስታውሶ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ግን ከመንግስት በተሰጣቸው ሩብ ሄክታር ማሳ የተሻሻለ የአፕል ዝርያ ችግኝ አፍልተው በመሸጥ በዓመት በግሉ 80 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግሯል። በየአመቱም ከ10 ሺህ በላይ የአፕል ችግኝ በማፍላት ለገበያ አቅርቦ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ የሚያገኘው ገንዘብ በመቆጠብም  በወረዳው  ለንግድ አገልግሎት በሚገነቡ ሁለት ህንጻዎች አክሲዎን እንዳለው ተናግሯል። የዚሁ ወረዳ የኩልውሃ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ምንይችል ገዳሙ በበኩሉ የአፕል ችግኝ አፍልቶ በመሸጥ ኑሮውን የተሻለ ማድረግ መቻሉን አመልክቷል። አምስት ሆነው በመደራጀት በአፕል ችግኝ ማፍላት ስራ ከተሰማሩ አምስት ዓመት እንደሞላቸው የገለፀው ወጣት ምንይችል በየመቱ ከ30 ሺህ በላይ ችግኝ በማፍላት ለገበያ እንደሚያቀረቡ ጠቁሟል፡፡ አንድ የአፕል ችግኝም ከ10 እስከ 25 ብር እንደሚሸጡ ተናግሯል። ከአፕል ችግኝ ሽያጭም በየዓመቱ በግሉ እስከ 120 ሺህ ብር በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርቷል። ወጣቶቹ መንግስት ከሰጣቸው ከግማሽ ሄክታር በላይ ማሳ በተጨማሪ ከግለሰቦች ተከራይተው እየሰሩ መሆኑንም አስረድቷል። በቀጣዩ የክረምት ወቅት የሚተከል ከ32 ሺህ በላይ ችግኝ ለገበያ ለማቅረብ የማፍላት ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግሯል። የደባይ ጥላት ግን ወረዳ የረጥባ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ዘውዲቱ አስማረ  ከጓደኞቿ ጋር በመደራጀት የአፕል ችግኝ በማፍላት ተጠቃሚ መሆኗን ገልፃለች። ከዚህ በፊት ለሁለት አመት ከግለሰብ ቤት ተቀጥራ ስትሰራ እንደነበር አስታውሳ ካለፈው አመት ጀምሮ ግን በአፕል ችግኝ ማፍላት ተደራጅተው ስራ በመጀመር 30 ሺህ ብር ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ተናግራለች። በዚህ አመት ደግሞ ስራውን የተላመዱት በመሆናቸው ደረጃውን የጠበቀ ችግኝ ማፍላታቸውንና ከችግኝ ሽያጭም ከ60 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚጠብቁ ጠቁማለች። የዞኑ ግብርና መመሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ተሾመ በላይ በበኩላቸው በዞኑ የአፕል ልማትን ለማስፋፋት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው። በተደራጁ ወጣቶችና በአርሶ አደሮች በመጭው የክረምት ወራት የሚተከል ከ220 ሺህ በላይ የአፕል ችግኝ ተፈልቶ ለተከላ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። በተፈላው ችግኝም 220 ሄክታር በላይ ማሳ ለመሸፈንና ከ8 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በልማቱ ለማሳተፍ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል። ችግኙን በማፍላት ላይ ያሉት ቀደም ሲልና በዚህ ዓመት የተደራጁ 240 ወጣቶችና አርሶ አደሮች መሆናቸውን ባለሙያው ገልፀዋል። በዞኑ በሚገኙ 12 ወረዳዎች ከ650 ሄክታር በላይ መሬት በአፕል ተክል የተሸፈነ ሲሆን ከ20 ሺህ በላይ አርሶአደሮች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም