በደቡብ ወሎ እና ደሴ በኮሮና መከላከል የልየታ ስራ 654 ሺህ ቤቶችን ማዳረስ ተቻለ

58

ደሴ፣ ግንቦት 2/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር በተካሄደ ቤት ለቤት የኮሮና መከላከል የልየታ ስራ 654 ሺህ ቤቶች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር የግብረ ኃይሉ ፀሃፊ አቶ አብዱልሃሚድ ይመር  የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከሚያዚያ 15/2012 ዓ.ም  ጀምሮ የቤት ለቤት ልየታ ስራ መካሄዱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በሁሉም ክፍለ ከተሞች 120 የጤና ባለሙያዎች  ከበጎ ፍቃደኞች ጋር ባከናወነው የልየታ ስራ  54 ሺህ ቤቶች ማዳረስ ችለዋል።

በተደረገው የአሰሳ ስራም 47 ግለሰቦች የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክና ቀላል የመተንፈሻ ችግር ያለባቸው ሆነው መገኘታቸውን ጠቅሰው፤ የምርመራ ናሙና ለመውሰድ በጤና ባለሙያ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው ዙር የልየታ ስራ ትናንት መጠናቀቁን ያመለከቱት አቶ አብዱልሃሚድ  ቀጣዩ ዙርም  እንደሚካሄድና ለዚህም 115 በጎ ፍቃደኛ የመረጃ ምንጮች በመሆን በየቀጠናው መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

የዞኑ  ግብረ ኃይል ፀሃፊ አቶ አንተነህ ደምመላሽ በበኩላቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት 700 ሺህ ቤቶችን ለማሰስ ከሚያዚያ 24/2012 ዓ.ም ጀምሮ የቤት ለቤት ልየታ ስራ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

በ24 ወረዳዎች ከአንድ ሺህ 500 በላይ የጤና ባለሙያዎችን በማሰማራት በአስር ቀናት ውስጥ  ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ  600 ሺህ ቤቶችን ማዳረስ እንደተቻለ አመልክተው ከነዚህም  ከ200 የሚበልጡ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክና የመተንፈሻ ችግር ያለባቸው  መገኘታቸውን አስረድተዋል።

ወደ ለይቶ ማቆያ ለመውሰድ የቫይረሱ ምልክት ጎልቶ የታየባቸውም የጤና ባለሙያ ክትትል በማድረግ በአቅራቢያቸው  ባሉ የምርመራ ማዕከላት  ናሙናቸውን ለማስመርመር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ህብረተሰቡም ከጤና ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅቶ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው" ያሉት አቶ አንተነህ ወረርሽኙን ለመከላከል በየቀበሌው መዋቅር ተዘርግቶ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ቤት ለቤት የሚደረገው አሰሳ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከፍተኛ ሚና ያለው ከመሆኑም ባሻገር የሚገመቱትን ወደ ለይቶ ማቆያ ለመውሰድና ፈጥኖ ለመመርመር እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡

የቤት ለቤት ልየታ ስራው በሙቀት መለኪያ መሰሪያ ጭምር ታግዞ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም