በአሁኑ ወቅት የቀጣናው ቀዳሚ ትኩረት ኮቪድ-19 እና የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝን መከላከል መሆኑን ኢጋድ ገለጸ

65

ግንቦት 2/2012 (ኢዜአ) በአሁኑ ወቅት የቀጣናው ቀዳሚ ትኩረት ኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) እና የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝን መከላከል መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ገለጸ።

ከኢስትአፍሪካን ጋዜጣ ጋር ቆይታ የነበራቸው የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንደተናገሩት፤ የኢጋድ ቀዳሚ ትኩረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የበረሃ አምበጣ የሚያደርሰውን የሰብል ውድመት መከላከል ነው።

ዋና ፀሐፊው ኢጋድ በቀጣናው ፈጣን ምላሽ የሚፈልጉ ጉዳዮች ምላሽ እንዲያገኙና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር የሚያስችል ለውጥ እንደሚተገበር ገልጸዋል።

ኮቪድ-19 የሚያስከትለውን ጫና ለመከላከልና በቀጣይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የኢጋድ አባል አገሮችን የማስተባበር ስራ በኢጋድ በኩል እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይም የቀጣናውን የምግብ ዋስትና ለከፋ አደጋ የሚያጋልጠውን የበረሃ አንበጣ ወረራ መከላከል የኢጋድ ትኩረት እንደሆነም አመልክተዋል።

ኢጋድ የቀጣናው ህዝቦችን ኑሮ ለማሻሻል ጥረት እያደረገ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ወርቅነህ፤ የወጣቶችና ሴቶችን አቅም ማጎልበት፣ የተፈናቃዮችን መብት ጥበቃ ማጠናከር፣ የአርብቶ አደሮችን ህይወት ማሻሻል እና የአካባቢና ተፈጥሮ ጥበቃ ስራዎች ኢጋድ የሚያከናውናቸው ስራዎች እንደሆኑም ተናግረዋል።

እጅግ ተለዋዋጭ የሆነ ሁኔታ በሚታይበት በዚህ ቀጣና በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ሰላምና ጸጥታ ግንባታ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መታየታቸውን ገልጸው፤ ይህንን ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ችግር የዓለም ዓቀፍ ችግር ቢሆንም በቀጣናው የሚኖረው ጫና የከፋ እንደሚሆን በመግለጽ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

ቀጣናው እነዚህ ችግሮች ቢኖሩበትም ከፊት የተደቀነው የቀጣናው አደጋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የሚያስከትለው ተጽዕኖ እንደሆነ አስረድተዋል። ችግሩ ብዙዎችን ስራ አልባ እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በመሬት መንሸራተትና ጎርፍ አደጋ የተነሳ ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታም ሌላው ፈታኝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

''240 ሚሊዮን ህዝብ ያለው ቀጣናው በርካታ የወጣቶች ቁጥር መያዙ ዕድል ነው'' ያሉት ዋና ጸኃፊው፤ ይህንን ዕድል መጠቀም ካልተቻለ የሚያስከትለው ቀውስ ከባድ መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህ ደግሞ ቀጣናዊ ትስስሩን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣናው ሰላምና ጸጥታ ዙሪያ እንዲሁም የህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በኢጋድ እየተሰሩ ስላሉ ስራዎችም ከጋዜጣው ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም