በኢሉአባቦር ዞን ከ119 ሚሊዮን በላይ ምርጥ የቡና ችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው

76
መቱ ሰኔ 28/2010 በኢሉአባቦር ዞን በዘንድሮ ክረምት ወራት ከ119 ሚሊዮን በላይ ምርጥ የቡና ችግኝ ተከላ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የባለስልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ ንጉሴ እንደገለጹት የቡና ችግኝ ተከላው እየተካሄደ ያለው በዞኑ 13 ወረዳዎች ውስጥ ነው። በቡና ተከላው ከ200 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን እስካሁን ባደረጉት እንቅስቃሴ ከ50 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ተክለዋል፡፡ በዚህም 15 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን ገልጸው የቡና ችግኝ ተከላ ሥራው ሲጠናቀቅ 35 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ይለማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። አቶ አዲሱ እንዳሉት ዘንድሮ ፈልቶ ለተከላ የተዘጋጀው የቡና ችግኝ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በዘጠኝ ሚሊዮን ብልጫ አለው። ምርጥ የቡና ዝርያዎቹ ከጅማ ምርምር ማዕከል የተለቀቁ ሲሆኑ ቀደም ሲል በሄክታር የሚገኘውን ከሰባት ኩንታል የማይበልጥ ምርት ከ12 እስከ 20 ኩንታል የማሳደግ አቅም እንዳላቸው አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡ በዞኑ በአሌ ወረዳ ገርበ ዲማ ቀደሌ አርሶ አደር አለማየሁ ሽፈራው ባለፉት 15 ቀናት ግማሽ ሄክታር በሚሆን ማሳቸው ላይ ከ1 ሺህ በላይ የቡና ችግኝ ተክለው እየተንከባከቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመቱ ወረዳ ቡሩሳ ቀበሌ አርሶ አደር ተርፋ ረጋሳ በበኩላቸው ከሌሎች የግብርና ምርቶች በበለጠ ለቡና ልማት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡ በክረምት ወቅቱ በቡና ለመሸፈን ካዘጋጁት ግማሽ ሄክታር መሬት በአብዛኛው ላይ የቡና ችግኝ መትከላቸውንም ተናግረዋል፡፡ በኢሉ አባቦር ዞን ከ160 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ምርት እየለማ መሆኑን ከባለስልጣኑ የተገኘ መረጃ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም