በደቡብ ክልል ከበልግ አዝመራ 128 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል

50

ሐዋሳ ግንቦት 01/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በተያዘው የበልግ አዝመራ ከ128 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ። 

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ለኢዜአ እንደገለጹት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የበልግ እርሻ ውጤታማ ለማድረግና የምርት እጥረት እንዳይከሰት እየተሰራ ነው።

የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ በበልግ አዝመራ መዘናጋት እንዳይፈጠር ከክልል እስከ አርሶ አደሩ ድረስ በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ እየተሰራ መሆኑን  ጠቁመዋል።

በክልሉ በዋናነት በበልግ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ የሚመረተውን ቦቆሎና ሌሎች የአዝርዕት ሰብሎች በተፈለገው ልክ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የመሬት ዝግጅት ተደርጓል ።

ከ195 ሺህ ኩንታል በላይ የምርት ማሳደጊያ ግብአትም ቀርቧል።    

በዚህ እንቅስቃሴ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቅሰዋል።

ከልማቱም ከ128 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ነው አቶ ዳንኤል ያመለከቱት።

ከዚህ በፊት በእርሻ ወቅት በአርሶ አደሩ ዘንድ የተለመዱ እንደ ደቦ፣ አንድ ለአምስትና መሰል ንክኪ የሚፈጥሩ አደረጃጀቶች በማስቀረት ከቤተሰብ አባላትጋር ብቻ በመሆን በየዕለቱ ማሳውን በመጎበኘትና የቅርብ ክትትል በማድረግ ምርታማነቱን የሚያሳድግበት አሰራር አንዲከተል ተደርጓል ።

የበረሃ አንበጣና የመጤ ተምች ክስተት ለምርትና ምርታማነት መቀነስ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ትንበያዎች ማመለካታቸውን ያነሱት አቶ ዳንኤል ክልሉ ከፌዴራልና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የኬሚካልና ሌሎች የመከላከያ ዜዴዎች ለመጠቀም ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ፍቅረየሱስ አሸናፊ ዝናብ ቀድሞ በመዝነቡና አየር ንብረቱ የተስተካከለ በመሆኑ አርሶ አደሩ ከቫይረሱ ራሱን እየጠበቀ የእርሻ ሥራውን ተግቶ እንዲያከናውን ግንዛቤ ተፈጥሯል።

በዚህ መነሻ በከተማዋና አካባቢዋ  1 ሺህ 800 ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ገልጸው ከምርት ይዘት የተነሳው ትንበያ መሰረት በአማካይ በሄክታር ከ70 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

 በሐዋሳ ከተማ  የአላሞራ ቀበሌ አርሶ አደር እንድሪያስ   በላቸው በሰጡት አስተያየት ከሁለት ሄክታር በላይ መሬት የተለያዩ ሰብሎች በመዝራት የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ ማቀዳቸውን ይገልጻሉ።

በግብርና ባለሙያዎች ምክር መሰረት ምርታማነትን ለማሳደግ መሬትን ደጋግሞ ማረሳቸውና የተለያዩ ግብአቶችን መጠቀማቸውንም አስረድተዋል።

እራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ቦቆሎና ሌሎች ሰብሎች በመዝራት የተሻለ ምርት ለማግኘት ትኩረት ማድረጉን የተናገረው ደግሞ ሌላኛው የቀበሌው ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር ተሻለ ቱንጋሞ ነው።

የእርሱ መኖር ለሌሎችም ጭምር መሆኑን የተናገረው አርሶ አደሩ ከእርሻ ልማቱ በተጓዳኝ  እጅ መታጠብና ማህበራዊ ርቀትን እንዲጠብቁ ትምህርት እንደሚሰጥም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም