ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት ለተሸጋገሩ አርሶ አደሮች ድጋፍ ይደረጋል...የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት

109

አዳማ፤  ግንቦት 1/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮች በሚሰማሩበት መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ በቴክኖሎጂ፣ በግብዓት አቅርቦትና በፋይናንስ እንደሚደግፋቸው የክልሉ መንግስት ገለፀ።

የኦሮሚያ ክልል የዘንድሮውን የኢንቨስትመንት ቀን ምክንያት በማድረግ ለ2 ሺህ 481 አርሶ አደሮችና ኢንተርፕራይዞች ዛሬ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ሰጥቷል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ተወካይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ በመገኘት ለአርሶ አደሮቹ የኢንቨስትመንት ፍቃድ አስረክበዋል።

አቶ ፍቃዱ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩት አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂ፣ በግብዓት አቅርቦትና በፋይናንስ አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ያገኛሉ ብለዋል።

መንግስት የግብርና ዘርፉን ከማዘመን ባለፈ ወደ ኢንቨስትመንት ለሚሸጋገሩ አርሶ አደሮች የመካናይዜሽን መሳሪያዎች፣ የፋይናንስ አቅርቦትና ከቀረጥ ነፃ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን እንዲያስገቡ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ አርሶ አደሩ ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ገበያ ተኮር ምርት እንዲያመርትና በቀጥታ ወደ ውጭ ሀገር መላክ እንዲችል ሁኔታዎች እየተመቻቹ ይገኛሉ ብለዋል።

በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆነ ምርት በጥራትና በብዛት አርሶ አደሩ እንዲያመርት የመካናይዜሽን አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የከተማ ቤትና መሬት ብቻ በባንክ በማስያዝ የብድር አገልግሎት ይሰጥ ነበር ያሉት አቶ ፍቃዱ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ መሬቱን በማስያዝ እንዲበደር አሰራሩ እየተከለሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተሞች አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው በሚካሄደው ኢንቨስትመንት የሚፈናቀሉ ሳይሆን በመሬታቸው አክስዮን የሚገቡበት አሰራር መመቻቸቱንም አስረድተዋል ።

የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጁላ ለማ እንደገለጹት ግንባር ቀደም አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ ለማስቻል እየሰራን ነው ብለዋል።

በዛሬው እለት የኢንቨስትመንት ፍቃድ የተሰጣቸው አርሶ አደሮች 1 ሺህ 481 ናቸው ያሉት ምክትል ሃላፊው፤ 1ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ናቸው ።

በተለይ የኢንቨስትመንት ፍቃድ አግኝተው በአግሮ ፕሮሰሲንግ ፣በአገልግሎት ፣በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርናና ሌሎች መስኮች የሚሰማሩ አርሶ አደሮች ከ77 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ ብለዋል።

ለኢንቨስትመንት የሚውል ከ5ሺህ 700 በላይ ሄክታር መሬት ለአርሶ አደሮቹ መሰጠቱን የተናገሩት ምክትል ሃላፊው ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አላካ ሲንብሩ እንደተናገሩት በዞኑ 58 አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት ተሸጋግረው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ዞኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ በተለይ ለአግሮ ፕሮሰሲንግና ለአገልግሎት ዘርፍ የሚሆን መሬት ማዘጋጀቱን ጠቅሰው አርሶ አደሩ በመንግስት የተዘጋጀለትን አማራጮች መጠቀም አለበት ብለዋል።

የኢንቨስትመንት ፍቃድ ካገኙት አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ ዘኑ ደጉ በሰጡት አስተያየት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ፍቃድ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በትምህርትና አገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል ፍቃድ ከክልሉ መንግስት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

በክልሉ ከሚገኙት ከ13 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች መካከል ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች መሆናቸው ተጠቅሷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም