በግድቡ ምንጣሮ የሚያከናውኑ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲቀርቡ ተጠየቀ

87

አሶሳ ግንቦት 1 / 2012 ዓ.ም. (ኢዜአ)፡የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወረዳዎች የህዳሴውን ግድብ ውሃ የሚተኛበትን ቦታ ምንጣሮ የሚያካሂዱ ወጣቶችን በአስቸኳይ አደራጅተው እንዲልኩ የክልሉ ሥራ እድል ፈጠራና ልማት ኤጀንሲ ጠየቀ ፡፡ 

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም ለኢዜአ እንደተናገሩት ክልሉ የህዳሴው ግድብ ውሃ የሚተኛበትን አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ከሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. በፊት አስመንጥሮ ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ስራውን ለማስጀመር ክልሉ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የውል ስምምነትና ሌሎች ማስፈጸሚያ ሰነዶች ለፊርማ መዘጋጀታቸውን አስተረድቷል፡፡

ስራው ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት የጸዳ ለማድረግ የሠራተኞቹን ደህንነት የሚከታተሉና የንጽህና መጠበቂያ እና ሌሎችንም ግብአቶች የሚያቀርቡ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

የምንጣሮ ሥራው ከ1 ሺህ 200 በላይ ሠራኞች በላይ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በክልሉ የሚገኙ 20 ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ፍትሃዊነት በተሞላበት መልኩ ሥራ አጥ ወጣቶችን አደራጅተው እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል ።

ይሁንና ወረዳዎቹ በስራው የሚሳተፉ ወጣቶችን አደራጅቶ በማቅረብ ረገድ መንጠባጠብ እንደሚታይባቸው ጠቁመዋል፡፡

“የችግሩ ምክንያት ደግሞ የወረዳ አመራሮች ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠት ነው” ያሉት አቶ በሽር ወረዳዎቹ በአጭር ጊዜ ሥራውን የሚያከናው ማህበራትን አሟልተው እንዲያቀርቡ አሳስበዋል፡፡

ወጣቹን በ70 ማህበራት የማደራጀቱ ሂደት ፍትሃዊነቱን በጠበቀ መልኩ መከናወን እንዳለበት በአቅጣጫው መቀመጡን ተናግረዋል ።

የሚመነጠረው ደን ውሃው በሚተኛበት ጉባ ወረዳ አወልቤጉ ቀበሌ እንዲከማች ይደረጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለሥራው 34 ሚሊዮን 146 ሺህ ብር በጀት ተመድቧል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም