የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል ልማት 10 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቀደ

141

 አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል ልማት 10 ሚሊዮን ዶላር ብድር መፍቃዱን አስታወቀ። 

በረጅም ጊዜ የሚከፈለው ብድር የተፈቀደው በቱሉ ሞዬ አካባቢ ለሚገነባው የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንዲውል ነው።

ፕሮጀክቱ  ኢትዮጵያ በታዳሽና በፍጥነት ጥቅም ላይ በሚውል የኃይል አቅርቦት ታግዛ  ኢኮኖሚዋንና የሕዝቧን አኗኗር እንደሚያሻሽል  ታምኖበታል።

በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ የመጀመሪያው የእንፋሎት  ኃይል አምራች  እንደሚሆንም ባንኩ ገልጿል።

“የታዳሽ ሃይል ቴክኖሎጂ ፈንድ በዚህ ፕሮጀክት በመሳተፉ ደስተኛ ነኝ።በረጅም ጊዜ  ክፍያ የተፈቀደው ብድር አገሪቱ የኃይል አቅርቦት አማራጯን እንድታሰፋ ያግዛታል።በተጨማሪ አገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ የያዘችውን ግብ እንድታሳካ ያስችላታል" በማለት በአፍሪካ  ልማት ባንክ የአየር ፀባይ ለውጥና የአረንጓዴ እድገት  ዳይሬክተር አንቶኒ ኒዮንግ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የ 50 ሜጋዋት የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ዲዛይን፣ ግንባታ ፣የሙከራ ሂደት፣የኃይል አቅርቦት ስርጭትና ማስተላለፍ ተግባራት ይከናወኑበታል።

ፕሮጀክቱ 11 ኪሎሜትር የሚረዝም የማስተላለፊያ መሥመር እንደሚዘረጋለትም  ተመልክቷል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ ዋና የኢንቨስትመንት ኦፊሰርና የታዳሽ ኃይል ስፔሻሊስት አንቶኒ ካሬምቦ  ፕሮጀክቱ አረንጓዴ ልማትን ለማስፋፋትና ለ600 ሰዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር   አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም