ሀገሪ በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የግብርና ምርቶች የማቅረብ ፀጋ ቢኖራትም በአግባቡ እየተጠቀመችበት እንዳልሆነ ተገለጸ

89
አዳማ ሚያዚያ 30/2010 ሀገሪቱ በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑና የተፈጥሮ ይዘታቸውን የጠበቁ የተለያዩ የግብርና ምርቶች የማቅረብ ፀጋ ቢኖራትም በአግባቡ እየተጠቀመችበት እንዳልሆነ ተገለጸ፡፡ የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ተወካይ ዶክተር ኢያሱ አብረሃ እንዳሉት የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ተፈጥሮአዊ ይዘታቸውን የጠበቁ በመሆናቸው በዓለም ገበያ ያላቸው ተፈላጊነት ከፍተኛ ነው ። ይሁን እንጂ ዘርፉን በእውቀት ፣በተነሳሽነትና በቴክኖሎጂ ታግዞና ዳብሮ ስላልተመራ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሪ እየተገኘ አለመሆኑን ገልጸዋል። "አይቮሪኮስት ከካካዋ ምርት ብቻ በዓመት በአማካይ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ስታገኝ ኢትዮጵያ ግን ከሁሉም የግብርና ምርቶች የምታገኘው ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ መጠን ከ3 ቢሊዮን ዶላር የዘለለ አይደለም "ብለዋል ። ዋነኛው የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሆነው የቡና ምርት  ባለፉት 15 ዓመታት ያሳየው አማካይ እድገት 1 በመቶ ብቻ እንደሆነ ያመለከቱት ዶክተር  ኢያሱ የኢትዮጵያን ተሞክሮና ባለሙያዎች ጭምር ተጠቅመው በቅርብ ጊዜ የቡና ልማት ስራን ያከናወኑት እነቬትናም ረጅም ርቀት መጓዝ እንደቻሉ ጠቅሰዋል። "ምርቱን በብዛትና በጥራት ማቅረብ አልቻልንም እንጂ የገበያ ተፈላጊነቱ አልጠፋም"  ያሉት ዶክተር ኢያሱ በቅርቡ ለሙከራ ወደ አውሮፓ የተላከው የአቦካዶ ምርት ከሌሎች ሀገራት በተፈጥሮአዊ ይዘቱ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል። ከየቦታው ተሰባስቦ የተላከው 20 ቶን አቦካዶን የተመለከቱ የገበያ ባለድርሻ አካላት በአንድ ጊዜ 20 ኮንቴይነር አቦካዶ እንዲቀርብላቸው ቢጠይቁም ዘርፉ ስላልተሰራበት ምርቱን እንደሚፈለገው ማግኘት እንዳልተቻለ አመላክተዋል። የሀገሪቱ የበርበሬ ምርት በጀርመንና በሌሎች የአውሮፓ ገበያዎች በይዘቱ ተቀባይነትና ተመራጭነት ቢኖረውም በግብይቱ ሰንሰለት ውስጥ እጃቸውን ያስገቡ ጥቂት ግለሰቦች ክብደት እንዲጨምርላቸው ውሃ አርከፍክፈው የላኩት በርበሬ ለአደጋ ተጋልጦ እንደነበርም አስታውሰዋል። ውሃ የተጨመረበት በርበሬ ሻግቶ ከፍተኛ አፍላቶክሲን የተባለ የመርዛማ ኬሚካል መጠን እንደተገኘበትም ጠቁመዋል፡፡ በገበያ ላይ ተፈላጊ ከሆኑ የጥራጥሬ ምርቶች በተጨማሪ በሀገሪቱ በብዛት ሊመረቱ የሚችሉ ጦስኝና ኦክራ የመሳሰሉ ምርቶችም በዓለም ገበያ ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ መሆኑንም ዶክተር ኢያሱ ጠቅሰዋል። ኦክራ በጋምቤላ ክልል በስፋት የሚመረትና ለካንሰር በሽታ መድኃኒት ቅመማ አገልግሎት የሚውል ተፈላጊ  ሰብል ነው ተብሏል ። በጋምቤላ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ባለሙያ አቶ አብዱልራህማን ሁሴን በበኩላቸው ኦክራ ከቃሪያ ጋር የሚመሳሰል አረንጓዴ ሰብል መሆኑን ጠቅሰው "አንድ እግር ኦክራ እስከ15 የሚደርሱ ዘለላዎች  ይኖሩታል "ብለዋል ። ኦክራ ለተለያዩ ምግቦች ማባያ ሆኖ ከማገልገሉም በላይ ለሆድ ድርቀት ፣ ለምግብ ፍላጎት መጨመርና ለካንሰር መድሃኒት መቀመሚያ ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል ። ሰብሉ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ምርት መስጠት የሚችል ፣ ብዙ የውሃ ፍላጎት የማይጠይቅና በሔክታር እስከ 45 ኩንታል  ምርት የሚሰጥ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል። " አንድ ኩንታል የኦክራ ምርት እስከ 4 ሺህ ብር ያወጣል " ያሉት ባለሙያው በጋምቤላ ክልል ከሚገኙ 14 ወረዳዎች በ12ቱ እንደሚመረት አስረድተዋል። ሰብሉ ባለፈው ዓመት በ314 ሔክታር መሬት መልማቱን ያስታወሱት ባለሙያው ዘንድሮ ወደ 600 ሔክታር ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ምርቱ በብዛትና በጥራት ለዓለም ገበያ የሚቀርብበትን እድል እንዲፈጠር የፌዴራልና የክልሉ ኃላፊዎች በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙም ከባለሙያው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል  ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም