አንድ አካል አንድ ህዝብ…

86
በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ) ሐጎስ ገብረህይወት የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳለ ነው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግጭትን ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ከኤርትራ እንዲወጡ ሲደረግ ቤተሰቦቹ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱት። ወላጆቹ አስመራ ውስጥ ለሰላሳ ዓመታት ኖረዋል። እሱን ጨምሮ ስድስቱ ልጆቻቸውም ተወልደው ያደጉት አስመራ ካምፖቦሎ የሚባል ሰፈር ነበር። የደረሰው ማህበራዊ ቀውስ ሲነሳ የእናት ከልጇ፣ የባል ከሚስቱ፣ በአጠቃላይ አስከፊ የቤተሰብ መለያየት ይታወሳል። ኑሯችን ህይወታችን ኤርትራ ነው ያሉ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ረግጠው ወደ ማያውቋት ኢትዮጵያ እንዲሄዱ ሲደረግ የእኔ ካሉት ነገር የመነቀል ያህል ነበርና ህይወትን እንደገና ከዜሮ ለመጀመር ተገደዋል። ኤርትራ እኤአ በ1952 ዓ.ም ከእናት ሃገሯ ኢትዮጵያ ጋር ከመቀላቀሏ በፊት የጠቅላይ ግዛት ስያሜን ይዛ በዚችው ሃገር ውስጥ ኖራለች። ከዚያም በኋላ በደርግ ዘመነ መንግስት የራስ ገዝ አስተዳደር በመባል የኢትዮጵያ የግዛት አካል ሆናም ዘልቃለች። ከ1983 ዓ.ም ለውጥ በኋላ ደግሞ የራሷን ነፃነት አውጃለች። ተገንጥላ ነፃነቷን ካወጀች ጀምሮ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ጥሩ ግንኙነት ይኖራል የሚል ግምት በመንግሥት በኩል እንደነበርና ይህን ታሳቢ ያደረጉ ነገሮችም ይከናወኑ እንደነበር በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዣዥ የነበሩት ሜ/ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት ያስታውሳሉ። እሳቤው ይህ ስለነበርም ድንበር ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደር ቁጥር በጣም አናሳና ድንበር ላይ ጦር አለ በሚያስብል ደረጃ እንዳልነበርም ያስታውሳሉ። "ጥሩ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ትብብር ይኖረናል ብለን አስበን ነበር። ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት የድንበር ጉዳይን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያን ወረረ። የድንበር ጉዳይን ለማስፈፀም ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር" የሚሉት ሜ/ጀነራል አበበ እውነተኛው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ነበር ይላሉ። የአንዲት ሃገር ልጆች ሆነው አንድ አካል አንድ አምሳል በመሆን  ለዘመናት የኖሩት ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች በባህል፣በቋንቋ አልፎ ተርፎም በሥጋ ዝምድና የተሳሰሩ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ተመልሶ መቀራረብና ወደ አንድነቱ ተመልሶ መምጣቱ የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ይገኛሉ። የሁለቱን አገራት የኋላ ታሪክ ስንመለከት ጥብቅ ቁርኝትን እናገኛለን፡፡ ሁለቱ አገራት በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት በላቀ ደረጃ የጋራ እሴቶች የገነቡ ናቸው፡፡ በተለይ በህዝቡ መካከል የነበረው መስተጋብር ሁለቱን አገራት በጥብቅ ያቆራኘ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቁርኝቱ በአንድ መንግስት ስር ለዘመናት መኖራቸው ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ህዝብ እርስ በርሱ መዋለዱና ተመሳሳይ ባህል፣ ቋንቋ፣ የአኗኗር ዘይቤ እና ማህበራዊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች በመሆናቸው ነው፡፡ አፍንጫ ሲነካ አይን ያለቅሳል እንደሚባለው የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች በክፉም በደጉም እርስ በርስ ሲደጋገፉ ስናየው የቆየነው ጉዳይ ነው። ባለፉት 18 አመታት ግን ይህ የሁለቱ አገራት ነባራዊ ሁኔታ ተቀይሮ ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት መግባታቸው ብቻ ሳይሆን ከግጭቱ በኋላም ቢሆን ችግሮቻቸውን ፈተው ወደ መልካም ጉርብትና ለመምጣትና ለዘመናት የቆየውን የሁለቱን አገራት ህዝቦች ጥብቅ ቁርኝት ለመመለስ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ በዚህ የተነሳም ሁለቱ መንግስታት እንደ ጠላት የሚተያዩና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እየተመለከተ አጠገቡ እንደተቀመጠ ፈንጂ የሚያይበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ለሚገኙ ህዝቦችም ሆነ በአካባቢው ለተሰማሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የዘወትር የቤት ስራ ሆኖ እቅልፍ የማያስተኛ የስጋት ቀጠና እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሁለቱ አገራት ግጭት ምክንያት ያለሃጢያታቸው ከሁለቱ አገራት ዜጎች  በመወለዳቸው ብቻ መብታቸውን ተነፍገው አንዱ የሌላውን ወገንና ዘመድ እንዲሁም ቤተሰቡን ለማየት ያልቻለበት አሳዛኝ ሁኔታ ሆኖ ቆይቷል። መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጉዳይ ተስፋ የሚያጭር ሀሳብ ተነሳ። የጠቅላይ ሚኒትርነት ሥልጣኑን የተቀበሉት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበዓለ ሲመታቸው ላይ ካሰሙት አነቃቂ ንግግሮችና ሐሳቦች መካከል በዓብይነት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የኤርትራን ጉዳይ የተመለከተ ነበር፡፡ በዕለቱ ንግግራቸው፣ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃ ከልብ እንፈልጋለን፡፡ የበኩላችንንም እንወጣለን፡፡ በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩ የሁለቱ አገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል፣ ልዩነታችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› የሚል መልዕክት ለኤርትራ መንግሥት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡ ከኢትዮጵያ በኩል እንዲህ ዓይነት የሰላም ጥሪዎችና የእንደራደር ጉትጎታዎች ላለፉት ዓመታት ወደ ኤርትራ ወገን ሲላኩ የነበረ ቢሆንም፣ ከኤርትራ ወገን የሚሰጠው ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ይህም የአልጀርሱ ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የማይተገበር ከሆነ መነጋገርም ሆነ መደራደር የማይቻል ነው የሚል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን የሰላም ጥሪ ተከትሎም ከኤርትራ ወገን የተገኘው ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ የሁለቱ አገሮችን ሰላምና ወንድማማችነትን ለመመለስ የሚቻለው፣ ኢትዮጵያ የአልጀርስ ስምምነትን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ስትፈጽም ብቻ መሆኑን፣ የሰላሙ ኳስ ያለው ኢትዮጵያ እግር ውስጥ ነው የሚል የተለመደው ምላሽ ከኤርትራ መንግስት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በቅርብ ጊዜ በተካሄደው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባም የሰላሙን ስምምነት እውን ለማድረግ በኢትዮጵያ በኩል እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ማናቸውንም ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ ኮሚቴው ባካሄደው ስብሰባ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበል አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጉባኤ ሲካሄድ ባደረጉት ንግግር ውስጥ የኤርትራን ጉዳይ አንስተው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ሁኔታ ‹‹ ሞት አልባ ጦርነት›› ሲሉ ገልፀውታል፡፡ ለዚህም ያቀረቡት ምክንያት ከ18 ዓመታት በላይ በአካባቢው የነበረው ነባራዊ ሁኔታ ማሳያ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ በነዚህ አመታት በአካባቢው ሰላም ባለመኖሩ ሁሌም ለጦርነት የሚያስፈልጉ ወጪዎች፣ ሁሌም ዝግጅት፣ ሁሌም ስልጠናና ውጥረት እንደነበር በማስታወስ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይም የስነልቦና ስቃይ ሆኖ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ባለፉት 20 አመታት ከኤርትራ ጋር በነበራት ግንኙነት ያተረፈችው ውጥረት ብቻ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ደግሞ ሁለቱም አገራት ተጎጂዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን የሰላም እጦት ለመፍታት ባለፉት ሁለት ወራት በተደረጉ ጥረቶች የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ሰላም በአፍሪካ ቀንድም ያስፈልገናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት እንዲስተካከል በኛ በኩል መስራት ያለብንን ስራ መስራት ይገባናል የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡ በሙሉ አቅማችንንና ጉልበታችንን ወደ ሰላም፣ ወደ ፍቅር እንዲሁም ወደ እርቅ ለማሸጋገርና የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ለማድረግ ሃሳባችንን ከሚከፋፍሉ ማናቸውም ነገሮች ሁሉ ወጥተን ፊታችንን ወደ ዋነኛው የአገራችን ጠላት ወደሆነው ድህነት በማዞር የኢትዮጵን እድገት፣ ሰላም እና ብልፅግና ለማረጋገጥ በጋራ እንድንሰራም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው ካነሷቸው ሃሳቦች መካከል አንዱ የሁለቱን አገራት ቀጣይ አቅጣጫ የሚያመላክት ነው፡፡ “በአስመራና በአዲስ አበባ መካከል አውቶቡስና ባቡር እንዲመላለስ እፈልጋለሁ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተስፋ ቃል አነጋገር ኢትዮጵያ ምን ያህል ለሁለቱ አገራት ግንኙነት ጠንክራ እየሰራች መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከኢትዮጵያ ጋር “ገንቢ ውይይት” ለመጀመር ወደ አዲስ አበባ ልዑካን ቡድን እንደሚልኩ  እንዳሳወቁ በኬንያ የኤርትራ አምባሳደር በየነ ርዕሶም በኩል ማሳወቃቸው ይታወቃል። በአገራችን “…በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” የሚል አባባል አለ፡፡ ይህ አባባል ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ አገራት የተረጋጋ ሰላም፣ ልማትና እድገት እንዲያስመዘግቡ ሰላም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ነገር ግን በርካታ ሰላም ፈላጊ በተሰበሰበበት ሁኔታ አንድም ቢሆን ሰላምን የሚያደፈርስ አካል ካለ ሰላም ሊመጣ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያም ዋነኛ አጀንዳዋ ሰላምን ማስፈንና በዚህም ሰላም ውስጥ የህዝቦችን እድገትና ብልፅግና ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ በውስጥም ሆነ በውጭ ያለውን የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ  ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ባለፉት ሁለት ወራት በአገራችን ሰላም እየሰፈነ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጭምር እስከማንሳት ደርሷል፡፡ ይህ ሁለቱን አገራት የማቀራረብ እንቅስቃሴ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በምስራቅ አፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ ላይ ለበርካታ አመታት ምርምሮችን ሲደርጉ የቆዩትና በእንግሊዝ ኪንግስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት  ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት  የሁለቱ አገራት ግጭት በአካባቢው ሰላምም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ያስከተለ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡ እነዚህ አገራት በግጭት ውስጥ መቆየታቸው የሁለቱን አገራት ህዝቦች በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳና የህዝቦችን ነፃነት የገደበ ተግባር ከመሆኑን ባሻገር የምስራቅ አፍሪካ አካባቢን ወደ አንድ ለማምጣት በሚደረገው አህጉራዊ ጥረትም እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ እነዚህ አገራት ግጭት ሊበቃ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ለሁለቱም አገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡ የሁለቱ አገራት ግጭት በሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንጻርም ያስከተለው ችግር ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ የወደብን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል፡፡ ኤርትራ የያዘችው አሰብም ሆነ የምፅዋ ወደቦች ለኢትዮጵያ የተሻለ ስትራቴጂያዊ ቦታዎች ናቸው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት በሰላም ላይ የተመሰረተ ቢሆን ኢትዮጵያ እነዚህን ወደቦች ለመጠቀም ያስችላታል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡ ኤርትራም ብትሆን ከዚህ ወደብ ይበልጥ ጥቅም ልታገኝ የምትችለው ከኢትዮጵያ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ እነዚህ ሁለት ወደቦች ለኢትዮጵያ በሚሰጡት ጠቀሜታ ኤርትራ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ማግኘት ያስችላታል፡፡ ይህንን የሰላም ጥሪ በመቀበልና ሊኖረው የሚችለውን ቀጠናዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ የኤርትራ መንግስት ሶስት አባላትን የያዘ የልኡካን ቡድን ባለፈው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ በመላክ ታሪካዊውን ግንኙነት አህዱ ብለው ጀምረውታል። በአጠቃላይ በሁለቱ አገራት መካከል ከ18 አመታት በላይ የዘለቀው “ሞት አልባ ጦርነት” ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የዳረገ ነው፡፡ በተለይ አፍሪካን በተለያዩ የልማት ኮሪደሮች ለማስተሳሰር ዘርፈ ብዙ የልማት ስራ እየተሰራ በሚገኝበትና በዚህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች በምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ በአካባቢው የሚፈጠር ሰላም ለሁለቱም አገራት ከሚሰጠው ጠቀሜታም ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ብሎም ለአህጉሩ  ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የተጀመረው የሰላም ግንኙነትን በማጠናከር እንደ ሐጎስ ያሉ ተበታትነው የሚኖሩ ወገኖች እንዲገናኙ ያደርጋልና ተጠናክሮ ይቀጥል መልዕክታችን ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም