ሴቶች ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ተቀናጅተው መስራት አለባቸው----አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

72
ባህር ዳር ሰኔ 27/2010 በአማራ ክልል በየደረጃው የሚገኙ ሴቶች መብትና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ የተጠናከረ አደረጃጀት ፈጥረው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ። “መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሴቶች የተደራጀ ትግል ወሳኝ ነው” በሚል መሪ ሃሳብ ክልል አቀፍ ዓመታዊ የሴቶች ኮንፈረንስ ዛሬ በባህር ዳር ተካሂዷል። በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደገለጹት አሁን እንደ ሀገር የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ የሴቶችን የተደራጀ አቅም ለማሳደግ ወሳኝ ነው። በየደረጃው በኃላፊነት ላይ የሚገኙ ሴት አስፈፃሚዎችና ወጣት ምሁራን ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጭነት እንዲመጡ መስራትና ማበረታታት፣ ስልጠና እንዲያገኙና በአደረጃጀት እንዲሳተፉ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አስረድተዋል። በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው ያለው አመራርም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል። “በተለይ ገጠር ለሚኖሩ ሴቶች፣ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግና ያለ አግብብ መሬታቸውን እንዳይነጠቁ የመሬት ህጉ ተሻሽሎ ወጥቶ እየተተገበረ ይገኛል” ብለዋል። “የክልሉ መንግስትም ሴቶች ያሉባቸው ችግሮች እንዲቀረፉ፣ አደረጃጀቶቻቸውን እንዲያጠናክሩ፣ መብት፣ ጥቅሞቻቸውንና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል” ብለዋል። የክልሉ ሴቶችና ህፃና ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፋንታየ ጥበቡ በበኩላቸው ሴቶች ተደራጅተው እርስ በእርስ በመረዳዳትና አቅማቸውን በመገነባባት በሚያደርጉት ስራ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን በየጊዜው እያሳደጉ ይገኛሉ። ይህም ሆኖ የአመለካከትና የአቅም ችግሮች ባለመቃለላቸው አሁንም በሴቶች ላይ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል። የመጡ ለውጦችን ለማስቀጠልና ያጋጠሙ ችግሮችን ለይቶ በቀጣይ ለመፍታት ባለፉት ሁለት ወራት በየደረጃው የሴቶች ኮንፈረንሶች ተካሂደው ችግሮች መለየታቸውን ጠቁመዋል። ከተለዩ ችግሮች መካከልም የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ በሚፈለገው ልክ አለመሆን፣ የተቀናጀ ተግባር ተኮር ትምህርት በአግባቡ አለመተግበር፣ የልጅነት ጋብቻን በታሰበው ልክ አለማስቀረትና ሌሎች ይገኙበታል። ችግሮችን ለማቃለልም ቢሮውና በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በቀጣይ ተቀናጅተው በመስራት የሴቶች አደረጃጀቶችን የመደገፍና የማጠናከር ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል። ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል ከደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ዘቢባ አህመድ ህገ-መንግስቱ ከወንዶች ዕኩል የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል። “በሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በኩል ውስንነት ያለ ቢሆንም ህገ-መንግስቱ ያረጋገጠልንን መብትና ጥቅም አደረጃጆቶቻችንን በማጠናከር መብቶቻችንን ለማስጠበቅ በቀጣይ ራሳች እንሰራለን” ብለዋል። በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ የአሪጋና ሸራ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ጠጀ ዋለ በበኩላቸው ችግሮችን ሴቶች ራሳቸው ታግለው በመፍታት መብትና ጥቅማቸውን ማስጠበቅ እንጂ ሌላ አካል እንዲሰራላቸው እንደማይጠብቁ ተናግረዋል። ለአንድ ቀን በተካሄደው ክልል አቀፍ ኮንፈረንስ ላይም ከክልል እስከ ቀበሌ የተወጣጡ 600 የሚሆኑ ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም