ፍትሃዊና ተደራሽ የንግድ ስርዓት ለመገንባት የዘርፉ አካላት በባለቤትነት መንቀሳቀስ አለባቸው---የንግድ ሚኒስቴር

58
ባህርዳር ሰኔ 27/2010 የሀገሪቱን ልማት የሚደገፍ ፈጣን፣ ፍትሃዊና ተደራሽ የሆነ የንግድ ስርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የዘርፉ አካላት በባለቤትናነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አሳሰቡ። "ዘመናዊ የንግድ ስርዓት ለፈጣን ኢኮኖሚ እድገት"  በሚል መሪ ሃሳብ ስድስተኛው የአማራ ክልል የንግድ ቀን ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተከብሯል። ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደገለፁት የንግድ ስርዓቱን ከልማዳዊ አሰራር በማላቀቅ ዘመናዊነትን የተላበሰ እንዲሆን የንግድ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ይህም ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን የንግድ ማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ህጋዊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች እንዲስተካከሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም መሻሻል ቢታይም አሁንም የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ አናሳ መሆን፣ የምርት ጥራት መቀነስ፤ በገበያ ተወዳዳሪ አለመሆንና የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት በንግድ ዘርፉ መሻገር ያልተቻሉ ችግሮች ናቸው። በዘርፉ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ፣ ግልፅ፣ ፍትሀዊና ተደራሽ እንዲሁም ጤናማ የንግድ ስርዓት ለመገንባት የዘርፉ ተዋናኞች በባለቤትነት መንቀሳቀስ አለባቸው "  ብለዋል። የክልሉ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ  ከ49 ሺህ 500 በላይ ነጋዴዎች ያለ ንግድ ፈቃድ ሲሰሩ ተገኝተው የማስተካካል ስራ መከናወኑን ገልጸዋል። የውጭ ንግድ እንቅስቃሴውን ለማበረታታት በተደረገው እንቅስቃሴም ከክልሉ ወደተለያዩ የውጭ ሃገራት ከተላኩ የሰብል፣ የእንስሳትና አሳ፣ የማዕድንና የኢንዱስተሪ ምርቶች ከ251 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል። "ይህም ከክልሉ አቅም አንፃር አነስተኛ እንደሆነና  የንግድ እንቅስቃሴው ዘመናዊነትን የተላበሰ አለመሆኑ ነው " ብለዋል። የንግድ ቀን ሲከበር በንግድ ማሻሻያዎች  ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና በዘርፉ ህጋዊ ንግድ እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ለባረከቱ አካላት ተገቢውን እውቅና ለመስጠት ያለመ ነው ተብሏል። በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ የመጡት  አቶ ያረጋል አይቸው በሰጡት አስተያየት የንግድ  ቀን መከበሩ  የንግድ ስራ የተከበረ ስራ መሆኑን ለህዝቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከማገዙም በላይ ነጋዴውን የሚያበረታታና ውድድር የሚፈጥር እንደሆነ ገልፀዋል። እሳቸው በተሰማሩበት የቡና ንግድ ተጨማሪ እሴት ታክስ በመሰብሰብ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አመልክተው፤ ተመሳሳይ ነጋዴዎች በህገወጥ መንገድ መንቀሳቀሳቸው በንግዳቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸውም ጠቁመዋል። ንግድ በልማድ የሚመራ ስራ ሳይሆን በእውቀትና በእቅድ የሚሰራ በመሆኑ የነጋዴውን አቅም በተከታታይ ማጎልበት እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡ በበዓሉ ወቅት የክልሉ ንግድ እድሎች፣ ፈተናዎችና መፍትሄዎች በሚል ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።በዘርፉ የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩ ነጋዴዎች፣ ባለሙያዎች፣ ተቋማትና የንግድ ዘርፍ ማህበራት የምስክር ወረቀትና ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም