በደቡብ ህዝቦች ክልል የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁ ተገለጸ

97
ሀዋሳ ሰኔ 27/2010 በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ለሶስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ዛሬ በሰላም መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊው ዶክተር እሸቱ ከበደ እንደገለጹት ፈተናው  ከሶስት ሳምንት በፊት መሰጠት ሲገባው በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ተራዝሞ ቆይቷል፡፡ የነበረው የጸጥታ ችግር እየተሻሻለ በመምጣቱ የተራዘመው ክልላዊ ፈተና ከሰኔ 25/2010 ጀምሮ ሲሰጥ ቆይቶ በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም 336 ሺህ 933 ተማሪዎች መፈተናቸውን ያመለከቱት ኃላፊው "አለመረጋጋቱ የፈተና ፕርግራሙን ከማዛባት ውጭ በትምህርት ስራ ላይ ያሳደረው ጫና የጎላ አይደለም" ብለዋል፡፡ ከጌዴኦ ዞን ተፈናቅለው ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄደው የነበሩ ተማሪዎችን ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊ ጥበቃ በማድረግና ግብዓት በማቅረብ ተመልሰው እንዲፈተኑ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ በሃዋሳ ከተማና በወላይታ ሶዶ ከተማም ተፈጥሮ በነበረው ችግር ተፈናቅለው በትምህርት ቤቶች ተጠልለው የሚገኙ ተማሪዎች ባሉበት እንዲፈተኑ ተደርጓል፡፡ በተማሪዎች ዘንድ በራስ የመተማመን ውስንነት መኖሩን የጠቀሱት ኃላፊው " ከአምናው  ጋር ሲነፃፀር ኩረጃና መረባበሹ አልተስተዋለም" ብለዋል፡፡ ሀሰተኛ መልስ ይዘው ለማጭበርበር ሲሞክሩ የተገኙና ለሌላ ተማሪ የተፈተኑ ግለሰቦች ተደርሶባቸው ፈተናቸው እንዲሰረዝ መደረጉን አመልክተዋል፡፡ የአስረኛና የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች በክረምት በጎ ፈቃድ በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ዶክተር እሸቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም