"የትኛውም አካል የአገውን ህዝብ የፖለቲካ አጀንዳው ማስፈጸሚያ ሊያደርገው አይችልም" ... አቶ አዲሱ መኮንን

93

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 29/2012( ኢዜአ) ''የትኛውም አካል የአገውን ህዝብ የፖለቲካ አጀንዳው ማስፈጸሚያ ሊያደርገው አይችልም" ሲሉ የአገው ብሄራዊ ሸንጎ ምክትል ሊቀ-መንበር የነበሩት አቶ አዲሱ መኮንን ተናገሩ።

"ምርጫው እንዲራዘም የተወሰነው ውሳኔ ወቅቱን የጠበቀና አማራጭ የሌለው ነው"ብለዋል።

የሸንጎው ምክትል ሊቀ-መንበር የነበሩት አቶ አዲሱ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት "ሸንጎው የወከለውን ህዝብ መብትና ጥቅም ከማስከበር ይልቅ የህወሃት አጀንዳ ማስፈጸሚያ ሆኗል"።

በአገው ህዝብ ላይ የተለያዩ በደሎች ሲፈጸሙ እንደነበር የገለፁት አቶ አዲሱ ሸንጎው የህዝቡን መብትና ጥቅም በማስጠበቅ እኩል የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ነበር ይላሉ።

ይሁንና በተለይ ''የሸንጎው ሊቀ-መንበር ከህወሃት ጋር ባላቸው ልዩ ቅርበት የወከሉትን የአገው ህዝብ ረስተው በህዝቡ ስም የህወሃት አጀንዳ አስፈጻሚ ሆነዋል'' ነው ያሉት።

ይህን በመቃወምም እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የሸንጎው ስራ አስፈጻሚ አባላት በተደጋጋሚ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥያቄ ቢያቀርቡም መፍትሄ ባለመምጣቱ ሸንጎውን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያታቸው ''የአገው ህዝብ የማንም አጀንዳ አስፈጻሚ መሆን የለበትም የሚል ነው''።

የሸንጎው ማዕከላዊ ኮሚቴ ሊቀመንበሩ በተደጋጋሚ ወደ መቀሌ የሚያደርጉትን ጉዞ ሲቃወም እንደነበር ና ሸንጎው የተነሳለትን ዓላማ የሳተ መሆኑን ቢያሳውቅም መፍትሄ አለመምጣቱን ገልጸዋል።

ግለሰቡ የወከሉትን ህዝብ በማይመጥን መልኩ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የአገው ህዝብ በሸንጎው ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር አድርጓል ነው የሚሉት።

አቶ አዲሱ ''ሸንጎው የወከለውን ህዝብ መብትና ጥቅም እንዲያስጠብቅ ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ትግላችንን ግን አናቋርጥም'' ብለዋል።

'የአገው ትግል በአገዎች ብቻ የሚደረገው መሆን መቻል አለበት' ያሉት የቀድሞው ምክትል ሊቀመንበር የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ትግላቸውን እንዲሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው እንዲራዘም የወሰነው ውሳኔ ወቅታዊና አማራጭ የሌለው ነው ሲሉ አቶ አዲሱ ይገልጻሉ።

አቶ አዲሱ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከግብጽ ጋር በሌላ መልኩ ደግሞ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ትንቅንቅ ውስጥ ገብታለች ሲሉም ጠቅሰዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት ከፖለቲካ ጨዋታ በመውጣት በአገር ስሜት መተባበርና ችግሩን በጋራ መወጣት ላይ ከማተኮር ይልቅ የራስን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ መሯሯጥ ኢ-ሰብዓዊነት ነው ብለዋል።

ወረርሽኙ በህዝብ ህይወትና ጤና ላይ የሚያደርሰውን ቀውስ ግምት ውስጥ በማስገባት ምርጫውን ለማራዘም የተወሰነው ውሳኔ አማራጭ የሌለው ነው ብለዋል።

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ የአገውን ህዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ጥር 5 ቀን 2011 ዓ ም መመስረቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም