የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ሚድዋይፎችና ነርሶች ይበልጥ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

80

 አዲስ አበባ  ሚያዝያ 29/2012 (ኢዜአ)ሚድዋይፎችና ነርሶች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ከመከላከል በተጓዳኝ የእናቶችንና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ይበልጥ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ። 

የዓለም የጤና ድርጅት የፈረንጆቹን 2020 “የሚድዋይፎች ና ነርሶች ዓመት” እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።

ጉዳዩን አስመልክቶም የኢትዮጵያ 'ሚዲዋይፎችና ነርሶች ማህበር' ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚድዋይፎችና ነርሶች ከአጠቃላይ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር 50 በመቶ የሚሆነውን እንደሚሸፍኑም ነው በዚህ ወቅት የተገለጸው።

በኢትዮጵያ ደግሞ 70 በመቶ የሚሆኑት የጤና ሰራተኞች ሴቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ አካል በመግለጫቸው የዓለም የጤና ድርጅት በ2030 በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚወልዱ እናቶች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑትን በህይወት የማስቀጠል ግብ ማስቀመጡን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የእናቶችን ሞት በመቀነስ ረገድ በርካታ ስኬቶች መመዝገቡን ጠቁመው፤ "አሁንም ቢሆን በቀን እስከ 30 የሚደርሱ እናቶች በወሊድ ወቅት ህይወታቸውን ያጣሉ" ብለዋል።

ከ10 ዓመት በኋላ ይህን ቁጥር ወደ አምስት ዝቅ ለማድረግ እቅድ መያዙንም አውስተዋል።

በመሆኑም ሚድዋፎች ዓመቱን ሲዘክሩ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ይበልጥ ሃላፊነታቸውን በመወጣት መሆን እንዳለበት ነው ያብራሩት።

በተጨማሪ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚድዋይፎች ቁጥር ለመጨመር በትኩረት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ነርሶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ታፈሰ በቀለ በበኩላቸው ዓመቱ የነርሲንግ ሙያ መስራች የሆኑት ፍሎረንስ ናትንጌል የተወለዱበት 200ኛ ዓመት የሚዘከርበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለነርሶች ልዩ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።

"ነርሶች ለራሳቸው ህይወት ሳይሳሱ እስከ ጦር ሜዳ ድረስ በመዝመት ጭምር ህይወት ሲያስቀጥሉ ቆይተዋል፤ እያስቀጠሉም ይገኛሉ" ብለዋል።

"ወቅታዊውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመከላከል ረገድም ነርሶች የፊት መስመር ተሰላፊ ናቸው" ሲሉም ነው የተናገሩት።

በመሆኑም ለዚህ ውለታቸው እውቅና እንዲሁም በጤናው ሴክተር ላይ ተገቢውን ቦታ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ዓመቱም ይህን ታሳቢ በማድረግ እንደተዘጋጀ በመጠቆም።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ታላላቅ ስኬቶች የነርሶችና ሚዲወይፎች ሚና ጉልህ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ናቸው።

በእነዚህ ሙያዎች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ካልተደረገ በ2030 በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘጠኝ ሚሊዮን የነርሶችና ሚዲዋይፎች እጥረት እንደሚከሰት አስታውሰው፤ "መንግስት ይህን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ያደርጋል" ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር የነርሶችንና ሚድዋይፎችን የሙያ ጥራትና የስራ ከባቢ ለማሻሸል ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሚሰራም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም