የነገም ሰው ለመሆን

99

የነገም ሰው ለመሆን ከሚስባህ አወል /ኢዜአ/ 

በወርሃ መጋቢት አጋማሽ ነው፡፡ከምኖርበት ሳንሱሲ ሸክላ መስጊድ አካባቢ ወደ አንበሳ ከተማ አውቶቡሶች መናኸሪያ ስደርስ ለሦስት ያህል ዓመታት ያላየሁት ትርምስ ተመለክትኩ።

የዚያኑ ያህል አውቶቡሶቹም ያለ ፋታ ይመጣሉ። ይሄዳሉ፡፡

በተለይ ወደ ፒያሳ የሚያቀናው ቁጥር 19 አውቶቡስ ከሕዝቡ ቁጥር ጋር የሚፎካከር ይመስላል።  ትርምሱ ግን አይቋረጥም።

የአካባቢው ወጣቶች በትላልቅ በርሜሎች ያን ህልቁ መሳፍርት እጁን ለማስታጠብ ደፋ ቀና ይላሉ።

''አንዳንዱ አሁን ነው ቤት ታጥቤ የመጣሁት።አልታጠብም'' ይላል። ወጣቶቹ ''አይደለም መታጠብ አለብህ'' ሲሉት የሚፈጠረው እሰጥ አገባ ዓይነት ንትርክ በራሱ ትዕይንት ነው።

ዛሬ በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ መልዕክቶች በቴሌቪዥን የምትከታተለው ትንሿ ልጄ ''ርቀትህን ጠብቅ '' ከኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ጣቢያ ያገኘቸውን ዕውቀት ተጠቅማ በምትልበት ዘመን  የእጅ መታጠብን ጥቅም ያልተረዳ ሰው ለማግኘት መቸገሩ ይደንቃል።

የአገሪቱ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ወጣቶች ዘመኑን ለማጥፋት የተነሳውን ጠላት ለመመከት እያደረጉ ባለው ጥረት ይሄ ሁሉ ትርምስና የ''ታጠብ ታጥቤያለሁ'' ጭውውት ባላስፈለገ ነበር።

ኮሮና በኢትዮጵያ ተከሰተ ከተባለበት ወር የመናኸሪያው አስተባባሪዎችም ተሳፋሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲሰለፉ አንዱ ተሳፋሪ ከሌላው እንዲራረቅ ቀለም በመቀባት በሰልፍ እንዲቆሙ ያደረጉት ጥረት በአብዛኛዎቹ መንገደኞች ሲከበር አልተስዋለም።አንዳንዱ የገባው አይመስልም። አንዳንዱ ደግሞ በዚህ ዓይነት ተሰልፎ መቆምን የፈለገው እንዳማይመስል ከፊቱ ያስታውቃል።ተሰላችቷል፡፡

እንደ ዘንዶ በተጥመለመለው ሰልፍ ርቀቴን ጠብቄ ተሰለፍኩ፡፡ ሰልፉን ሲያዩት ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢሆንም፥በመናኸሪያው አስተባባሪዎች  ቅልጥፍናና  በአውቶቡሶቹ ፈጣን እንቅስቃሴ ታግዞ ወደ መድረሻዬ የማደርገውን ጉዞ ቀጠልኩ።

በሰልፉ መሃል አሁንም የለመድነው ''ተጠጋጉ'' የሚል መልዕክት እየተደጋገመ መሰማቱ ዘመኑ ያመጣውን ርቀት መጠበቅ የሚል ከበሽታ መጠበቂያ ስልት ሲጋፋው ተመልክቻለሁ።እንኳን ሁለት ሜትር አንድ ሜትር ብርቅ ከሆነበት ርቀታችን ይልቅ፤ ''ጣልቃ እንዳታስገቡ'' የሚለው ሥርዓት የማስጠበቅ መልዕክት ጎልቶ ሲሰማ ነበር።አስፈላጊነቱ ባያጠራጥርም፤ኮሮናን የመሰለ ሕዝብ አጥፊ ወረርሽኝ በገባበት ዘመን  ሥርዓት አክብሮ መሰለፍ እንደተከበረ ሆኖ፤ ርቀት መጠበቅን  መጋፋት አልነበረበትም።

አሁን በሳንሱሲ፤ በመገናኛ፣ በመርካቶና በሌሎች መናኸሪያዎች ላይ የአውቶቡሶቹና የሕዝቡ ቁጥር  ባለመመጣጠኑ ትርምሱ ቀጥሏል።ሌሎቹም ችግሮች አብረው ቀጥለዋል።በተለይ ቤት ቤት መቀመጥ አገርሽቶበት ኮሮናን ፍለጋ ወደ አደባባይ ወጥቷል።

ዛሬ  ኮሮናን ለመከላከል  የወጡ መመሪያዎች  በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ጭምር የተቻለ አይመስልም።ሁሉም ነገር የተዘነጋ ይመስላል!!

በሽታውን ለመከላከል በየአካባቢው የተጀመሩ እጅ የማስታጠብ ሥራዎች በአብዛኛው ቆመዋል። በየዓመቱ የሚከበረውን ''የእጅ መታጠብ ቀን''ን  የምንጠብቅ አስመስሎናል።

የእጅ ጓንትና የፊት ጭምብል ማድረግም ለጥቂቶች የተተወ እየመሰለ መጥቷል።ምንም እንኳን ጭምብሎቹ ገበያውን ቢያጥለቅልቁም።

ሕዝቡ ዛሬም በዚህ የአደጋ ወቅት የዘመቻ  አሰራርን  ከያዘበት አስተሳሰብ ውስጥ  አይመስልም። ጀምሮ መቋረጥ በደም ሥራችን የገባ የሚንከላወስ በሽታ  ሆኖብናል።ዓለምን ባናወጠው በዚህ ጊዜም  ከወረት ያለፈ ሥራ ያለመውጣታችን ሕይወት እንደሚያስከፍለን የዘነጋነው ይመስላል።

ዛሬ ላይ የሩቁን ገታ አድርገን ጎረቤቶቻችንን እንኳን መቃኘቱ በቂ ይመስላል።ጅቡቲ  እንዴት ነች? ኬንያና ሶማሊያ ምን ደርሰዋል?ሱዳንስ ምኑ ጋ ነው ያለችው? ብሎ ፍተሻ ማድረግ ያነቃናል ብዬ አስባለሁ።

በየደቂቃው እየጨመረና መረጃው እየተለዋወጠ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ከ3ነጥብ6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ማጥቃቱንና ከ265ሺህ በላይ ሕዝብ መሞቱን እየሰማን ባለንበት ኢትዮጵያውያን የምንጠብቀው በሕይወት መኖርን ነውና ወደሚነገረን እንመለስ።ከሌሎች እንማር። 

በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ወረርሽኝ ሲያጋጥም የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም።በእርግጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከደረሱበት ደረጃ አኳያ በዚህ ጊዜ ይህንን ያህል ጥቃትና ሞት ማጋጠሙ ኮቪድ19ን አስከፊ ቢያደርጉትም።

በአገራችን በተወዳጅነቱ ግንባር ደረጃ ከሚይዘው በሐዲስ ዓለማየሁ በተጻፈው ''ፍቅር እስከ መቃብር'' ውስጥ ዋናው ገጸባህሪ በዛብህ ወላጆች መንደር ላይ ተከስቶ ስለነበር የተስቦ(ወረርሽኝ) በሽታ ነው የሚያጠነጥነው ክፍል እንዲህ ቀርቧል፦

አባ ምህረቱ ወይዘሮ ውድነሸ በቤታቸው ጓሮ ተገኙ፡፡  

“እንደምን አደሩ አባታችን?”

“እኔ ቄስ ምህረቱ ነኝ እንዴት አደሩ እመት ውድነሽ?”

“እዚያብሄር ይመስገን እንደምን አደሩ አባቴ!” አሉ እመት ውድነሽ።

“እሰው አገር ሰንብቼ ሳልጠይቃችሁ ሰነበትሁ። በሽተኛው እንደምን ናቸው?”

“በሽተኛው? …. በሽተኛውማ …. አረፈ “ አሉ እመት ውድነሽ ወደ አባ ምህረት ለመሄድ መንገድ እየፈለጉ።

“አረፉ አየ ሰው አየ ትልቅ ሰው! እዚያው ይሁኑ እመት ውድነሽ የተከተሎዎ አይታወቅምና አይምጡ መቼ አረፉ ? አሉ አባ ምህረቱ እመት ውድነሽ ወደሳቸው ለመሄድ መሞከራቸውን ሲያዩ ወደሁዋላ እየሸሹ።''

በዚያ ዘመን የነበረው ኅብረተሰብ በነበረው ግንዛቤ ራሱን ለመጠበቅ ያደረገው ጥንቃቄ  ትምህርት  ሊሆነን  ይገባል፡፡

አባ ምህረቱ ርቀታቸውን ጠብቀው ስለበሽተኛው ከጠየቁ በኋላ  በሽተኛው ከሞቱ ሁለት ቀናት ማለፋቸውን ያረጋገጡበትና በኋላም  ቀብሩን ለማስፈፀም የተጠቀሙበት ዘዴ ቀላል አልነበረም፡፡

የአቶ ቦጋለ መብራቱ የነፍስ አባት መምህሬ ምህረቱ ሠራተኛቸው ልከው ከእመት ውድነሽ ጋር ብቻ በመሆን ተጋግዘው መቃብር ማድረሳቸውና ቀባሪዎቹንም “ሬሳውን አስቀምጣችሁ።ተመለሱ!”በማለት ያስተላለፉት መልዕክት የዚያን ዘመን ትውልድ ወረርሽኝን መከላከል እንደቻል ያስተምረናል፡፡

ዛሬም የዚህ የሰለጠነና የረቀቀ ዘመን ትውልድ ራሱንና ሌሎችንም መጠበቅ እንደሚችል ማሳየት ይጠበቅበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም