የተመድ የአደገኛ ዕጾች እና ወንጀል መከላከል ጽህፈት ቤት ለፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

71

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2012 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የአደገኛ ዕጾች እና ወንጀል መከላከል ጽህፈት ቤት ለፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ግምቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡ 

ድጋፉ በፌዴራል እና በክልሎች የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) እንዲከላከሉ የሚረዳ መሆኑም ተመልክቷል፡፡  

በድጋፍ ርክክብ ስነስርዓቱ በኢትዮጵያ የተመድ የአደገኛ ዕጾች እና ወንጀል መከላከል ጽህፈት ቤት ተጠሪ ኦፊሰር አቶ አብርሃም አያሌው እንዳሉት፤ ጽህፈት ቤቱ በተለያየ ጊዜ በህግ ጥላ ስር ለሚገኙ ታራሚዎች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

ዛሬ ያደረገው ድጋፍ በፌደራል እና በክልሎች ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲከላከሉ የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡   

56 የሙቀት መለኪያ መሳሪያ፣ 940 ሊትር ሳኒታይዘር እና 230 ሳጥን የአፍ መሸፈኛ ማስክ በድጋፉ መካተታቸውንም አቶ አብርሃም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የተለያዩ ሰነዶችን በማዘጋጀት በማረሚያ ቤት የሚገኙ ወገኖች ራሳቸውን ከበሽታው እንዲከላከሉ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ይህን ድጋፋቸውንም አጠናክረው እንሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡

የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሱን የተረከቡት የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሰው ሃብት ልማት ፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ያረጋል አደመ በበኩላቸው ድጋፉ ለታራሚዎች የሚውል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮሮናቫይረስ በአገሪቱ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ በርካታ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለኮሚሽኑ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

የተመድ የአደገኛ ዕጾች እና ወንጀል መከላከል ጽህፈት ቤት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም በማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ወገኖች ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላለፈዋል፡፡  

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት ለመከላከል ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናና ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም