የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች የንፁህ ውሀ መጠጥ ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ

106
ጅግጅጋ ሰኔ  27/2010  የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች ለረጅም ጊዜ ሳይፈታ የቆየው የንፁህ ውሀ  መጠጥ  ያለማግኘት ችግር መንግስት እንዲፈታላቸው ጠየቁ፡፡ የከተማው ነዋሪ ተወካዮች በጉዳዩ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስት ጋር ለመነጋገር ባለፉት ቀናት በጅግጅጋ ከተማ ተወያይተዋል፡፡ ከነዋሪው ተወካዮች መካከል አቶ በድል ሳላድ እንዳሉት  የከተማው ህዝብ ለመጠጥነት የሚጠቀመው ውኃ ከዋቢ ሸበሌ ወንዝ ነው፤ ይህም  ድፍርስና ንጽህና የጎደለው  በመሆኑ ለውሃ ወለድ በሽታ ተጋልጠዋል፡፡ ሌላው የከተማው ነዋሪ ተወካይ  አቶ መሐመድ አደም በበኩላቸው "የከተማው አየር ሁኔታ ሞቃታማ በመሆኑ ያለ ውሀ መኖር አስቸጋሪ አድርጎታል "ብለዋል፡፡ ንጽህና ከጎደለው ድፍርስ  ውሀ ከወንዝ በአህያ እያመላለሱ መኖር በጣም ከባድ መሆኑን የገለፀው ወጣት አሕመድ ሐሰን አሁን መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መወያየት መጀመሩ ተገቢ መሆኑን  ተናግሯል፡፡ ለረጅም ጊዜ ሳይፈታ የቆየው የንፁህ የውሀ መጠጥ ችግር የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እልባት እንዲሰጣቸው ነዋሪዎቹ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ጠይቀዋል፡፡ በክልሉ ውሀ ሀብት ልማት ቢሮ የጎዴ ንፁህ የውሀ መጠጥ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መሐመድ ኢብራሂም በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመፍታት ከአፍሪካ ልማት በብድር በተገኘ ሁለት መቶ ሰላሳ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ በዋቤ ሸበሌ ወንዝ የውኃ ማጣርያ ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል፡፡ " ፕሮጀክቱ ለሃያ ዓመት የከተማዋን ንፁህ የውሀ መጠጥ እንዲሸፍን የታቀደ ነውም "ብለዋል፡፡ በ2011 በጀት ዓመት መግቢያ ላይ ግንባታውን የሚጀምረው ፕሮጀክቱ  በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ እና ሰማንያ አራት ኪሎ ሜትር የሚሆን አጠቃላይ የውሀ ማስተላለፊያ ቱቦ በመስራት ችግሩ  እንደሚፈታ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ የክልሉ ውሀ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሀሊን መሐመድ በበኩላቸው በጎዴ ያለውን የመጠጥ ውሀ ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡን የመፍትሄው አካል እንዲሆን ማወያየታቸውንና በዚህም መግባባት ላይ  መድረሳቸውን  ጠቅሰው በቅርብ ክትትል ለችግሩ  እልባት ለመስጠት  ድጋፋቸው አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም