በቤንች ሸኮ ዞን እየተከናወኑ ያሉ ግንባታዎች ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው

56

ሚዛን ሚያዝያ 27/2012 (ኢዜአ) በቤንች ሸኮ ዞን እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ፡፡

የዞኑ አመራሮች  በክልልና ፌዴራል መንግስት በአካባቢው  እየተገነቡ የሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የዞኑ  ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን እንደገለጹት በዞኑና በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡

"ፕሮጀክቶቹ ሲጠተናቀቁ ለዞኑ ህብረተሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው" ብለዋል።

በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ያሉ የግንባታ ፕሮጆክቶች መኖራቸውን የተናገሩትአቶ ፍቅሬ በተለያዩ ምክንያቶች ከተያዘላቸው ጊዜ አኳያ ግንባታቸው የተጓተቱ እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የሚዛን መናኸሪያ ፣ የሚዛን አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተሐድሶ ማዕከል ግንባታዎች መዘግየት ከሚታይባቸው እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

የሚዛን አማን አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ደግሞ ሌላው የግንባታ አፈጻጸም ክፍተት የታየበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፕሮጀክቶቹ መዘግየትም ለታለመላቸው ዓላማ እንዳይውሉና በህብረተሰቡ ዘንድ የቅሬታ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀላል ምክንያቶች የተጓተቱ ተለይተው በማጠናቀቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት እንዲበቁ  ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የዞኑ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሣሙኤል አሰፋ በበኩላቸው የአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተሀድሶ ማዕከል፣ የመናኸሪያና የምክር ቤት ህንጻዎች ግንባታ በፌዴራልና በክልል መንግስት በተመደበ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተካሄደ የሚገኙ እንደሆኑ አስረድተዋል።  

የአፈጻጸም ክፍተት የታየባቸውን ለይተው በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ ጥረት እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

በመስክ ጉብኝቱም የሣይት ፕላን የሌላቸው ግንባታዎች፣ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ በወቅቱ ከይዞታ አለማስለቀቅ ክፍተቶች መኖራቸው ተገምግሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም