ኤክስፖው አገር በቀል ተቋማት ከውጭ ድርጅቶች ልምድ እንዲያገኙ ማድረጉ ተገለፀ

73
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአይ ሲ ቲ ኤክስፖ በቢዝነስ ተቋማትና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙት እንዲሻሻልና አገር በቀል ተቋማት ከውጭ ድርጅቶች ልምድ እንዲያገኙ ማድረጉ ተገለጸ። ''በአይ ሲ ቲ ኢትዮጵያን ማሸጋገር'' በሚል መሪ ቃል በሚሌኒየም አዳራሽ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፍ የአይ ሲ ቲ ኤክስፖ ዛሬ ተጠናቋል። ኤክስፖው በቢዝነስ ተቋማትና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙት ለማሻሻል እንዲሁም ከውጭ አገር ድርጅቶች ጋር አገር በቀል ተቋማት እንዲገናኙና ልምድ እንዲቀስሙ አድርጓል ያሉት የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ ናቸው። በኤክስፖው 110 ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን አስታዋውቀል፤ 300 ሺህ የሚሆን ህዝብ በኤክስፖ ላይ ጉብኝት ማድረጉም ተገልጿል። በኢትዮ-ቴሌኮም ስፖንሰር አድራጊነት ሶፊያ የተባለችው ተናጋሪ ሮቦት በኤክስፖው ላይ መቅረቧም የዘርፉ ተመራማሪዎችን ለማበረታታት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል። በሮቦቷ አጠቃላይ ስራ ላይ ኢትዮጵያውያን ከ60 በመቶ በላይ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ኤክስፖው በቴክኖሎጂ ዘርፍ ትልቅ ልምድ ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሳተፉ እና እንዲያለሙ ግንኙነት ለመፍጠር ሁኔታዎችን ማመቻቸቱንም  አቶ  አብራርተዋል፡፡ ወጣት ተመራማሪዎችና የስራ ፈጠራ ባለቤቶች ሀሳባቸውን፣ ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ለህብረተሰቡ እና ለተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት አስተዋውቀዋል። ኤክስፖው የቢዝነስ ተቋማትን ከቴክኖሎጂ ጋር በማገናኘት ስራቸውን በአንድ የቴክኖሎጂ ማዕከል እንዲያከናውኑ የሚያደርጉበትን ልምድ ለማግኘት ይረዳልም ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ላለፉት ዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት የአይ ሲ ቲ ኤክስፖ ያዘጋጀች ሲሆን አለማቀፋዊ ኤክስፖ ስታዘጋጅ ግን ይህ ሁለተኛዋ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም