የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫን በሚመለከት በቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን የመፍትሄ ሀሳብ አፀደቀ

157

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2012 (ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኮቪድ 19 ምክንያት 6ኛውን ብሄራዊ ምርጫ ለማከናወን አለመቻሉን አስመልክቶ ከህግ፣ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን የመፍትሄ ሃሳብ በ25 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ 3ኛ ልዩ ስብሰባውን ዛሬ ሲያካሂድ የምክር ቤት አባላት በተለይ የምርጫ መራዘምን ተከትሎ የህግ ፈትህና ዴሞክራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው ሀሳብ ላይ የተለያዩ ሀሳቦችን በማንጸባረቅ ክርክር አድርገዋል።

ዓለም ዓቀፉ የኮረና ወረርሽኝ በኢትዮጰያ የሚያደርሰውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳት ለመቀነስ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ይታወቃል።

ለአብነትም በርካታ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው የእምነት ተቋማትን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘጉ በአስቸጓይ ጊዜ አዋጅ ተወስኗል።

የፖለቲካ ፓርቲ፣ የዕድርና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችም ከአራት ሰዎች በላይ እንዳይሰበሰቡ እገዳ ተጥሏል።

ወረርሽኙ በዜጎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ከመንግስት ባለፈ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ርብርብ እያደረጉ መሆኑም ግልጽ ነው።

ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሎ ቀነ- ገደብ ተቆርጦለት የነበረው ስድስተኛ ብሄራዊ ምርጫ በኮቪድ 19 ምክንያት ማካሄድ ስለማይቻል እንዲራዘም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለምክር ቤቱ ማቅረቡ ይታወቃል።

ምክር ቤቱም የውሳኔ ሀሳቡን በማጽደቅ ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የህገ-መንግስት የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርብ መምራቱ የሚታወስ ነው።

በዛሬው የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባም ቋሞ ኮሚቴው ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ በምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ የመከራከሪያ ሃሳቦች ተነስተዋል።

የቋሚ ኮሚቴውን የውሳኔ ሀሳብ ያቀረቡት አቶ አበበ ጌዴቦ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰዎች ህይወትና ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንና ከዚህም አልፎ ከባድ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫና እያደረሰ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

ወረርሽኙ በኢትዮጵያም የሚያደርሰውን ጫና ግምት ወስጥ በማስገባት በዜጎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ጥፋት እንደ ሉዓላዊ አገርም ቀጣይነት ፈታኝ ተግዳሮት መሆኑን መረዳት ተገቢ መሆኑንም አብራርተዋል።

በመሆኑም ''የምርጫው መተላለፍ ህገ-መንግስታዊ በሆነ አካሄድና የአገርን የህዝብን ህልውና ብሎም ሉዓላዊነትን ከተለያዩ ስጋቶች መከላከል በሚያስችል መልኩ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አጽንኦት መስጠት'' ይገባል ብለዋል።

ሆኖም በቀጣይ ወረርሽኙን መቆጣጠር ከተቻለ ምርጫውን ማካሄድ የሚቻል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የህገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄ ማቅረቡ ተገቢ መሆኑንም አብራርተዋል።

ቋሞ ኮሚቴው ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ አባላቱ የተለያዩ ሀሳቦችን አንስተዋል።

ህገ ምንግሰታዊ ትርጓሜ አያስፈልግም ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ገደብ መካሄድ አለበት ከሚሉት ጀምሮ ምክር ቤቱ ቀደም ሲል የህገ-መንግስት ጥሰት ሲፈጽም እንደነበር የሚያነሱ አስያየቶች ተደምጠዋል።

ምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን "የሕገ መንግሥታዊ ትርጉም" አማራጭ የውሳኔ ሀሳብ በ25 ድምጸ ተዓቅቦ በአምላጫ ድምጽ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የኢትዮጵያ መንግስት ከተላየዩ አገራት ጋር የብድር ስምምነት ለማድረግ የቀረቡትን ስድስት ረቂቅ አዋጆችም አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም