ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ 79ኛውን የአርበኞች የድል በዓል በማስመልከት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልእክት አስተላለፉ

70

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2012 (ኢዜአ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ  79ኛውን የአርበኞች የድል በዓል በማስመልከት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልእክት አስተላለፉ።

ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንኳን ለ79ኛው የድል ቀን በሰላም አደረሰን፡፡

በመላው ዓለም በተከሰተው የኮቪድ-19  ስጋት  የተነሳ  እንደለመድነው  በአርበኞች ሀውልት ዙሪያ አንድ ላይ ተሰባበስበን በዐሉን ማክበር አልቻልንም፡፡ ሆኖም ግን የእነዚያን የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆችን ዘመን የማይሽረው ተጋድሎ በመንፈስ አድምቀነው እንደምንውል እምነቴ ጽኑ ነው፡፡  

የዓለም የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ጮራ የሆነውን የአድዋ በዓልን የዛሬ ሁለት ወር አክብረናል፡፡ በተመሳሳይ የኩራትና የአይበገሬነት ከፍታ እንዲሁም መንፈስ  ላይ የሚያስቀምጠንን የሚያዝያ 27 የድል በዓልን አስበን እንውላለን፡፡፡፡ ይህን ቀን ስናስታውስም ብዙ የታሪክ ሰበዞች ተከታትለው ይቀመጣሉ፡፡

አድዋ ላይ ያላሰቡትን  ውርደት የተከናነቡት ፋሽስቶች ቂማቸውን ለመወጣት ቀን ሲቆጥሩ ከርመዋል፡፡ የታጠቁትን መሳሪያ ተማምነው ፤የጠነሰሱትን ባርነት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ለማንገስ ተማምለው ድንበር ጥሰው ገቡ፡፡ መጀመሪያ ገደማ ያሰቡት የሰመረላቸው መሰላቸው ፡፡ በኢትዮጵያውያን ላይ ያዘነቡት የሞት መዐት እድሜ ልካቸውን ከዚህች ምድር የሚነቅላቸው እንደሌለ ዋስትና አድርገው ወሰዱት፡፡ በከተማውና በገጠሩ የሞት ነጋሪት ጎሰሙበት፡፡

ብዙም ሳይቆይ ግን ታሪክ ተገለበጠ፡፡ ኢትዮጵያውያንን በቅኝ ግዛት ለማንበርከክ የተመመው የፋሽቶች ሠራዊት የወጠነውን ሳይጨርስ ግማሽ መንገድ ላይ ቀረ፡፡ ኢትዮጵያውያን እናትና አባት አርበኞች የሙሶሎኒን የአደባባይ  ድንፋታ እና የሠራዊቱን  እብሪት የጠዋት ጤዛ አደረጉት፡፡ የአድዋውን ቂም ለመበቀል ከ40 ዓመታት በኋላ የተወጠነው ዘመቻ በድጋሚ በአድዋ መንፈስ መና ቀረ፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ

ይህ የኢትዮጵያውያን በጨለማ ውስጥ ብርሀን መፈለግን ፤ በመከራ ውስጥ ተባብሮ ማንሰራራትን ፤ በጭንቅ ጊዜ ተስፋ ማድረግን በተለይ አሁን ለምንገኝበት ሁኔታ እጅግ በጣም አስፈላጊያችን ስንቅ ነው ብየ አምናለሁ፡፡

የአድዋ እና የአርበኞችን ድል መንፈስ እየታደሰ የሚቀጥል ህያው መንፈስ ማድረግ አለብን፡፡ ለዘላቂ የሀገራችን ጥቅሞች ልናውላቸው ይገባናል፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሳየነውን አንድነትና ታላቅ ህልም በሌሎችም ላይ እናባዛው፡፡ ዛሬ በተለያየ መልኩ የተደቀኑብንን ፈተናዎች ድል ለመንሳት እናውላቸው፡፡

ኮቪድ-19 የደቀነብን አደጋ ከማይታይ ጠላት ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡  የቫይረሱ ተለዋዋጭ ሁኔታ ሥራችንን ሁሉ ዱካውን ያጠፋ ጠላት ያህል ፈታኝና ውስብስብ አድርጎብናል፡፡ መመሪያ አክብረን ፤የሚጠበቅብንን ተወጥተን እስከተፋለምነው ድረስ ለመቆጣጠር ያለንን ዕድል ያሰፋዋል ፡፡ ከወረርሽኙ በኋላ የሚኖረውን ሁኔታ ከአሁኑ የተሻለ ለማድረግም  የቤት ስራችንን መጀመር ይኖርብናል፡፡

ዛሬ ያልሠራንበትን ነገ አናገኘውምና፡፡ የኢትዮጵያን የድህንትና የርሀብ ታሪክ ጨርሶ ለመለወጥ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ተቻችለን ፤ ተደማምጠን እና ተከራክረን የሀገራችንን ተስፋ ለማለምለም ቆርጠን እንነሳ፡፡ ይህን ስናደርግ የእነዚያ አይበገሬ ኢትዮጵያውያን አሻራ ህያው ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገራል፡፡ ያለንበትን ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ለዘላቂ እድገት እናውለው፡፡ የአድዋም ሆነ የአርበኞች ድል ከዚህ ውጭ የመጣ አይደለምና።

"መልካም የአርበኞች የድል በዐል" በማለት መልካም ምኞታቸውንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም