የምርጥ ዘር እጥረት እንዳጋጠማቸው የምሥራቅና ቄለም ወለጋ አርሶ አደሮች ተናገሩ

81

ነቀምቴ ሚያዝያ 26/2012 (ኢዜአ) እራሳቸውን ከኮሮና በመከላከል ለመጪው የመኸር ወቅት ለሚያደርጉት የእርሻ ዝግጅት የምርጥ ዘር እጥረት እንዳጋጠማቸው የምሥራቅና ቄለም ወለጋ ዞኖች አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በሁለቱ ዞኖች በመኸሩ ወቅት ከሚለማው ሰብል ውስጥ  በቆሎ ግንባር ቀደሙ ነው።

አርሶ አደሮቹ ኮሮናን ከመከላከሉ በተጓዳኝ የእርሻ ዝግጅት እያደረጉ ቢሆንም በተለይም የሚፈልጓቸው  ሊሙ፣ ሾኔና ዳሞት የሚባሉ የበቆሎ ዝርያዎች እጥረት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ የደንገሊ ጎንኬ ቀበሌ አርሶ አደር ሀብታሙ ዲባባ ለኢዜአ እንዳሉት ኮሮናን ለመከላከል ከመንግሥትና ጤና ባለሙዎች የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ እያደረጉ የእርሻ ዝግጅት ላይ ናቸው።

በአካባቢያቸው  የተላመዱ ሊሙ ሾኔና ዳሞት የሚባሉ የበቆሎ ዝርያዎች እጥረት እንዳጋጠማቸው ጠቅሰው  ለዘር ካዘጋጁት 2 ሄክታር መሬት  ውስጥ  ለግማሽ ሄክታር ብቻ የሚበቃ ዘር እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሌላው በጉቶ ጊዳ ወረዳ የኡኬ ቀበሌ ሞዴል አርሶ አደር ተመስጌን ኢፋ በበኩላቸው በኮሮና ምክንያት መዘናጋት እንዳይፈጠር ለጤንነታቸው ጥንቃቄ እያደረጉ 14 ሄክታር መሬት አለስልሰው ለዘር ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም  ያገኙት የበቆሎ ዘር ግን ለሁለት  ሄክታር የሚበቃ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፍቃዴ አክሊሉ ስድስት ሄክታር መሬት ለዘር አዘጋጅተው የዘር ችግር እንዳጋጠማቸው አመልክተዋል።

በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን ዳሌ ዋበራ ወረዳ የከረ ጄኖ ቀበሌ  አርሶ አደር ጋዲሣ ነገሪ ሁለት ሄክታር መሬት ለበቆሎ ዘር ቢያዘጋጁም ያገኙት የምርጥ ዘር በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ሌላው  አርሶ አደር ገበየሁ ጪብሣም በበኩላቸው የእርሻ መሬታቸውን ለዘር አዘጋጅው ያገኙት ምርጥ ዘር አነስተኛ በመሆኑ ወቅቱ እንዳያልፍባቸው ስጋት እንዳሳደረባቸው አመልክተዋል።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስፋው ሐምቢሣ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የአርሶ አደሩ ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልጸው "ከፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን የመጣ ችግር ነው" ብለዋል፡፡

ለምርት ዘመኑ ለዞኑ ከተጠየቀው 49 ሺህ 795 ኩንታል የተለያየ የበቆሎ ምርጥ ዝርያዎቹ ውስጥ እስካሁን  የቀረበው 16ሺህ ኩንታል ብቻ እንደሆነ  አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሩ በብዛት የሚፈልጋቸው የሊሙ፣ የሾኔና የዳሞት ምርጥ ዘር በቆሎ ከፍተኛ እጥረት የሚታይባቸው መሆኑን ጠቅሰው የተዘጋጀው የአርሶ አደሩ ማሣ ጦም እንዳያድር BH-546 በሚባል የበቆሎ ዝርያ ለመተካት ጥረት እየተደረገ  መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቄለም ወለጋ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦልብራይት ሁንዴሣ በበኩላቸው ከኮሮና ቫይሬስ ጋር በተያያዘ በክረምቱ እርሻ ላይ መዘናጋት እንዳይፈጠር  በአግባቡ እየተሰራ ቢሆንም የምርጥ ዘር እጥረት አጋጥሟል ብለዋል፡፡

ለዞኑ ከሚያስፈልገው 6 ሺህ 410 ኩንታል ምርጥ የበቆሎ ዘር አሁን የደረሰላቸው 3 ሺህ 752 ኩንታል ብቻ በመሆኑም ለምርት ዘመኑ ስጋት መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ የሚፈልጉት ምርጥ ዘር ሲያቀርብ የነበረው የፓዮኒር ምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅት ባለሙያ አቶ ጅጊ ቅጤሳ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ እስካሁን ወደ 18 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የሊሙ፣ የሾኔና የዳሞት ምርጥ ዘር በቆሎ መቅረቡን ተናግረዋል።

የቀረውንም ወቅቱ ሳያልፍ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በግል የምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅቱ ካልቀረበ በክልሉ የምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅት የበቆሎ ምርጥ ዘር  እንደሚሸፈን የየዞኖቹ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ጽሕፈት ቤቶች  ገልጸዋል።

በምሥራቅ እናቄለም  ወለጋ ዞኖች በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው 592ሺህ 281 ሄክታር መሬት ውስጥ 245ሺህ 745 ሄክታር  ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም