የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአገራዊ ችግሮች ቀዳሚ የመፍትሄ አካል መሆን አለባቸው

77

አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/ 2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ እንደ ኮቪድ-19 አይነት ቀውስ ሲፈጠር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቀዳሚ የመፍትሄ አካል መሆን እንዳለባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከአማካሪ ምክር ቤቱ ጋር በመተባበር “ከፍተኛ ትምህርትና ምርምር በዘመነ ኮቪድ-19” በሚል ርዕስ  የቪዲዮ ኮንፍረንስ አካሂዷል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንዳሉት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወረርሽኙ መግባቱን ተከትሎ ከኮቪድ-19 ጋር የተገናኙ ምርምና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ሰርተዋል።

የግንብዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት፤ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ማምረት፤ ትምህርት በተክኖሎጂ ለመስጠት የተለያዩ ድረ ገፆችን በማበልፀግ መፅሀፍት እንዲጫኑ ተደርጓል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች በለይቶ ማቆያነት እያገለገሉ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በተለይ የጤና ተቋማት ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ማከሚያ በመሆን አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።

በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተከሰቱ ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ  በመውሰድ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከአማካሪ ምክር ቤት አባል ዶክተር ተሾመ ይዘንጋው፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረጉ በርካታ ጥናትና ምርምሮች በኮቪድ-19 ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይሄ ደግሞ ትኩረቱን ሁሉ አንድ ጉዳይ ላይ በማድረግ በሌሎች የጤና ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር ሀብት ማሰባሰብ ይገባል ብለዋል።

ወረርሽኙ በዓለማችን የመጨረሻው ላይሆን ስለሚችል ቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮች ቢከሰቱ መወጣት የሚቻልባቸውን መንገዶች መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑም ተገልጿል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጥቅም ላይ የዋሉ የቴክሎጂ አማራጮችን ወስዶ ወደ ፊት መጠቀምና ምርጥ ተሞክሮ የሚባሉትን ለይቶ ማስፋት ያስፈልጋልም ተብሏል።

በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የየራሳቸው የልህቀት ማዕከል ሊኖራቸው እንደሚገባም ተገልጿል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ተቋማት የጀመሩት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለማጎልበት ምሁራን ድጋፈ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፤ መማር ማስተማርና ሌሎች ሥራዎችን በመለየት ወደ ሥራ መግባት የሚገባቸውን ለይቶ የአሰራር ስርዓት ይዘረጋል፤ ወደ ፖሊሲ የሚቀየሩትም ተለይተው ወደ ስራ ይገባሉ ብለዋል።

በቀጣይ ሊመጣ የሚችለውን ወረርሽኝ ለመቋቋም ምሁራንን ማዘጋጀት፣ ቴክኖሎጂዎችንና መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እንዲሁም ሃብት ማሰባሰብ እንጀምራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም