የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ከአራት ዓመት በፊት ኤሌክትሪክ ለማግኘት ክፍያ ቢፈጽምም እስካሁን መብራት አላገኘም

77
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ከአራት ዓመት በፊት ኤሌክትሪክ ለማግኘት ክፍያ ቢፈጽምም እስካሁን መብራት አለማግኘቱን ገለጸ። በደረቅ ወደቡ የወደብና ፋሲሊቲ ማስተባበሪያ ከፍተኛ ሲቪል መሃንዲስ ጋረደው አወቀ እንዳሉት፤ ሞጆ ደረቅ ወደብ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ለአገልግሎቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ቢከፍልም እስካሁን አገልግሎቱን አላገኘም። የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር ደረቅ ወደቡን በገነባው የስራ ተቋራጭ ወጭ መተከሉን የገለጹት መሀንዲሱ ችግሩ ከዚህ ውጭ መሆኑን ገልጸዋል። በተለያየ ጊዜያት ባለሙያዎች እንደሚመጡና ስራውን ከጀመሩ አንስቶ ለሁለት ዓመታት ያህል ከመመላለስ ያለፈ ስራ ሊሰሩልን አልቻሉም ብለዋል። ችግሩ እንዲፈታ ደጋግመን ጠይቀናል የሚሉት መሃንዲሱ፤ የሚመለከተው ተቋም በወቅቱ ችግሩን ባለመፍታቱ በደረቅ ወደቡ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ተዕጽኖ እያሳደረ እንደሆነም ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ደረቅ ወደቡ ባለፈው ሳምንት ላስመረቀው ከባቡር ላይ እቃ ማውረጃና መጫኛ ዘመናዊ የኮንቴነር ማንቀሳቀሻ ወይም አር ኤም ጂ ቴክኖሎጂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን አቅርቦቱ ባለመኖሩ በጄነሬተር እንደሚሰራ ተናግረዋል። ይህም ከፍተኛ የሀብት ብክነት እያሳደረ መሆኑ ተገልጿል። የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር በሁሉም ደረቅ ወደቦች የሚያጋጥም ችግር እንደሆነ የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጀት አመራሮች ተናግረዋል። ተቀማጭነቱን አዳማ ከተማ ያደረገው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደቡብ ምስራቅ ሪጅን በበኩሉ ችግሩ በቅርብ ቀናት እንደሚፈታ አስታውቋል። የቀጠናው ዋና ዳይሬክተር አቶ መልካሙ ደቢሳ በስልክ በሰጡት ማብራሪያ "ለተቋሙ አዲስ በመሆናቸው ችግሩ ለምን እስካሁን እንደዘገየ እንደማያውቁ" ገልጸው፤ ያም ሆኖ ችግሩን ለመፍታት ከደረቅ ወደቡ አመራሮች ጋር መነጋገራቸውን አውስተዋል። "ደረቅ ወደቡ የኛም ጉዳይ ነው" ያሉት አቶ መልካሙ፤ አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶ ቀሪ ስራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም