ምርጫ እንዲካሄድ ከማሰብ ለህዝብ ጤና ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ

67

ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 26/2012( ኢዜአ ) የኮሮና ቫይረስ በፈጠረው ስጋት ሀገራዊ ምርጫን ከማሰብ ይልቅ ለህዝብ ጤና ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ 

አስተያየት ሰጪዎቹ  ሀገራዊ ምርጫው  በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ መሰረት ማካሄድ እንደማይችል በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበው ምክረ ሃሳብ ተገቢ  መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ብሩክ ደጀኔ በሃዋሳ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ አሁን ላይ ከኮሮና ቫይረስ  ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ያለው ጫናና ስጋትን ለማቃለል  መስራት እንጂ ስለምርጫ ማሰብ አግባብነት እንደሌለው ይናገራሉ።

"ተመርጦ መምራትና መንግስት መሆን የሚቻለው ህዝብ ሲኖር ነው" ያሉት አስተያየት ሰጪው ቅድሚያ ለህዝብ ጤና ማሰብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ቫይረሱ በሰው ህይወት ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት አሳሳቢ በመሆኑ በዘላቂነት ለህዝቡ የሚጠቅሙና የሚበጁ ሃሳቦችን ለማመንጨት በሰከነ መንፈስ መወያየት ተገቢ መሆኑን አመልክተው " በቅድሚያ በሽታውን ለማጥፋት በሚቻልባቸው መንገዶች ርብርብ ይደረግ"  ነው ያሉት። 

የከተማው ነዋሪና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ አንድነት አለማየሁ በበኩሉ "በዓለም ላይ አሁን ሁኔታው አስቸጋሪና መገመት የማይቻል በመሆኑ ነገሮችን በውይይት በመፍታት ቅድሚያ ለጤና መስጠት እንጂ ምርጫ መካሄድ የለበትም "ብሏል፡፡

ህዝቡ ተረጋግቶ እንዲመርጥም ዕድል ሊሰጥ እንደሚገባና የኮሮና ወረርሽኝን መመከት እስኪቻል ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መቀጠል እንዳለበትም ተናግሯል።

አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ለህዝብ ጤንነት ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት ጠቅሰው ሀገራዊ ምርጫው በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ መሰረት ማካሄድ እንደማይችል ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ምክረ ሀሳብ  ተገቢ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ተመስገን አጋ ናቸው፡፡

"በተለይ መንግስት ለህዝብ ደህንነት ቅድሚያ መስጠት ስላለበት ለውይይት ክፍት በማድረግ የወሰደው አቋም ትክክል ነው "ብለዋል፡፡

ምርጫ ለማካሄድ አስቸጋሪ ሁኔታ በማጋጠሙ ምን ይደረግ በሚል መንግስት ለውይይት ያቀረባቸው አማራጮች መልካም እንደሆኑም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም