የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከቻይና ምን እንማር?

78


ቻይና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ልትቆጣጠረው ቻለች?
ኢትዮጵያ ከቻይና ልትወስድ የምትችለው የስኬት ተሞክሮ ምንድነው? የሚሉና የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በኢትዮጵያ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በቻይና የኢፌዲሪ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ማብራሪያ ሰጥተውናል።


ጥያቄ 1. ኮቪድ-19 በቻይና እንደተከሰተ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር ? እርስዎስ በወቅቱ የተሰማዎት ስሜት?


የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እ.አ.አ. በዲሴምበር 2019 መጨረሻ አካባቢ ተከስቶ ስርጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የሄደ በሽታ ነው። ይህ ወቅት ደግሞ ከጃንዋሪ 25 እስከ ፌብሩዋሪ 1 ቀን 2020 የቻይናውያኑ የዘመን መለወጫ ወይም SpringFestival ይከበር የነበረበትና በየአመቱ በአማካይ እስከ ስድስት መቶ ሚሊዮን ያህል ሰዎች በአለም ትልቁን የሀገር ውስጥ ጉዞ (Internal Migration) – (በቻይና ውስጥ ብቻ ማለት ነው)፤ የሚያደርጉበት ጊዜ ስለነበር ትልቅ መደናገጥና ከፍተኛ የጉዞዎች መስተጓጎልን አስከትሎ ነበር፡፡

እሱን ተከትሎ ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተባትና ወደ 11 ሚሉየን ዜጎች የሚኖሩባት የሁቤይ ክፍለ ሀገር ዋና ከተማ ዉሀን ከጃንዋሪ 23 ቀን 2020 ጀምሮ ማናቸውም አይነት የትራንስፖርትና የህዝብ እንቅስቃሴ ከከተማዋ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍልም ሆነ ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ከተማዋ እንዳይደረግና ነዋሪዎች ለመሰረታዊ አገልግልት ካልሆነ በቀር ከቤት እንዳይወጡ ተደረገ።

ከዛም በሁቤይ ክፍለ-ሀገር በተለይም በውሀን ከተማ በቫይረሱ የተያዙና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች በየቀኑ በመንግስት ለህዝቡ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ይፋ ይደረጉ ጀመር። ቀስ በቀስም ቫይረሱ ወደ ሌሎች የቻይና ክፍለ-ሀገሮችና ከተሞች - ቤጂንግን ጨምሮ፤ መሰራጨቱን ቀጥሎ ሀገር-አቀፍ በኋላም አለም አቀፍ ወረርሽኝ እስከ መሆን ደርሶ በአለም የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈና ሚሊዮኖችንም ያጠቃ አሳዛኝ ክስተት ለመሆን በቃ። ስለሆነም ስለቫይረሱ ብዙ በማይታወቅበት ሁኔታ ክስተቱ አስደንጋጭ፣ አስከፊና ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ጫና የሚፈጥር ነበር፡፡

ይሁንና ከመንግሥትና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ ሃሳቦችን በመከተል ራሳችንን ለመከላከል እቤት በመቆየትና ጥንቃቄ በማድረግ እዚህ ደርሰናል፡፡

ጥያቄ 2. በእርስዎ እይታ ቫይረሱ በቻይና እና ቻይናውያን ላይ ያደረሰው ተፅዕኖ እንዴት ይገለፃል?

ቫይረሱ በቻይና ከሰማንያ ሺህ በላይ ሰዎችን ያጠቃና ከእነርሱም ውስጥ ከአራት ሺህ በላይ ህይወት የቀጠፈ ወረርሺኝ ነው።የህክምና ተቋማቶቿና የጤና ባለሙያዎቿ ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ከረጅም አስርተ-ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደታች እንዲያሽቆለቁል ምክንያት መሆኑንም የተለያዩ ምንጮች እየገለጹ ይገኛሉ።

ይህም በዜጎች ህይወትና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ (የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ) እንዲሁም ማህበራዊ ክንውኖች (የትምህርት ቤቶች መዘጋትና የአገልግሎት ዘርፉ እንቅስቃሴዎችን በማዝቀዝ) አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ በሕዝብ ዘንድ እንቅስቃሴን በዝጋት የተለመደው ማህበራዊ ሕይወትን በመገደብ የሥነ ልቦና ጫና ፈጥሯል፡፡ችግሩን በሀገር ደረጃ በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ባደረጉት ርብርብ የተፈራው እና እንደተሰጋው ጉልህ ጉዳት ሳያስከትል ለመቅረፍ ችለዋል፡፡

ጥያቄ 3. ቻይናውያን ቫይረሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት መቆጣጠር ቻሉ ?


ቻይናውያን ቫይረሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቆጣጠር ያስቻላቸው በርካታ እርምጃዎች ቢኖሩም ተለይተው ሊጠቀሱ የሚችሉትን መጥቀስ ይቻላል፦


የጤና ምርመራና ሪፖርት ሥርዓት

ጠንካራ የሆነ ዕለታዊ የምርመራ፣ የክትትልና የሪፖርት ሥርዓት በመዘርጋት እያንዳንዱን የበሽታውን ሥርጭት የተመለከቱ ጉዳዮች በሁለም ባለድርሻ አካላት እንዲታወቁና አስፈላጊ እርምጃ በወቅቱ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡የሀገሪቱ የታክስ መስሪያ ቤት የድንገተኛ ጊዜ የጤና ክትትል ሥርዓት በሁለም የሀገሪቱ መውጫና መግቢያዎች በመዘርጋት፣ የዜጎችና የተጓዦችን የጤና ሁኔታ ለማወቅ ሙቀታቸውን መለካት፣ ምርመራ ማድረግና ዜጎች ወደ ከተሞች በሚገቡና በሚወጡበት ወቅት የሚጠቀሙት የጤና መግለጫ ካርድ ሥርዓቱን አሻሽሏል፡፡

በጠና ለታመሙ ሰዎች የጤና ክትትልና ህክምናን "አራት አካላትን ማቀናጀት" (four concentration) በሚል የታመሙ ሰዎችን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ ሀብትንና ለኮሮና ቫይረስ ብቻ የተለዩ ማዕከላትን በማቀናጀት በመሥራት፣ በሁሉም ከተሞችና ወረዳዎች ሆስፒታሎችን ለቫይረሱ ህክምና መስጠት በሚቻልበት ቁመና በመቀየር፣ የሆስፒታሎችን ቁጥር በመጨመር፣ የጤና ባለሙያዎችን በስፋት በማሰማራትና አማካሪ ኤክስፐርቶች ምክር እንዲሰጡ በማድረግ በጠና የታመሙ ሰዎችን ከሞት በማትረፍ ረገድ ቻይና ጠንካራ እንቅስቃሴ አድርጋለች።

በተለይም በውሃን ከተማ በ10 ቀናት ብቻ የተገነቡት ሁለቱ “ሆዎሸንሻን እና ላሸንሻን“ተብለው የተሰየሙ ሆስፒታሎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ጽኑ ህሙማንን ብቻ በማከም ቫይረሱን በመቆጣጠር እና በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
“ሆዎሸንሻን” ሆስፒታል አንድ ሺህ የህሙማን አልጋዎች ያሉት ሲሆን “ላሸንሻን” ሆስፒታል ደግሞ 1600 የህሙማን አልጋዎች አሉት። ሁለቱን ሆስፒታሎች 4000 የሀገሪቱ ጦር ኃይል የህክምና ቡድን ተረክቦ አገልግሎቱን በከፍተኛ ዲሲፕሊንና ጥንቃቄ ማበርከት ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል ዘመናዊ እና የቻይና ባህላዊ መድኃኒቶችን እንደየ አግባብነታቸው በመጠቀም (mutual complementarities of treatments) ታማሚዎችን በማከም ወረርሽኙን መቆጣጠር ችለዋል፡፡ ጠንካራ የበሽታ ሥርጭት ክትትል በታማሚዎች እና በማህበረሰብ ደረጃ በመዘርጋት የቫይረሱን ምንጭ መለየትና የተነጣጠረ (targeted) የመቆጣጠሪያ ስሌቶች ተፈጻሚ ማድረጓ፤ በብሔራዊ ደረጃ የሀገሪቱ የመንግሥት ምክር ቤት የቻይናዊያን አዲስ ዓመት አከባበር እንዲራዘም በማድረግ፣በሀገሪቱ በሁለም አካባቢዎች የሚካሄደ የተለያዩ ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው የስፖርት፣ ሲኒማ፣ ቲያትርና ሌሎች ሁነቶችን በማቋረጥ፣ የትምህርት ተቋማት ከአዲሱ ዓመት በኋላ የሚከፈቱባቸውን ጊዜያት በማራዘም፤ ትምህርት በበይነ-መረብ (online) እንዲሰጥ እየተደረገና ለሕዝቡ ዕለታዊ ኑሮ ወሳኝ የሆኑ ግልጋሎቶች ብቻ ክፍት እንዲሆኑ በማድረግ፤ የተለያዩ ተቋማት ሥራ የሚጀመሩባቸውን ጊዜያት በማስተካከል፣ የትራንስፖርት ድርጅቶች በሽዎች የሚቆጠሩ የኳራንቲን መቆጣጠሪያ በመግቢያና መውጫዎች ላይ በማቋቋም፣በሽታው በስፋት የታየበትን የሁቤ ክፍለ ሀገር የከተማ የህዝብ ትራንስፖርት፣የምድር ውስጥ የባቡር መሥመርና፣የረጅም ርቀት የመንገደኞች ጉዞ በጥብቅ የትራፊክ ሥርዓት እንዲመራ እና ሁሉም ዜጋ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲለብስ በማድረግ ቫይረሱ እንዳይሰራጭ አድርጋለች።


በቻይና መንግስት በከፍተኛ ዝግጅትና ትኩረት በየዓመቱ በማርች ወር የሚካሄደው የሕዝብ ሸንጎ እና የቻይና ሕዝባዊ የፖለቲካ ምክክር ኮንፍረንስ ለተወሰነ ጊዜ ተላልፏል።የታማሚዎችን የጤና ኢንሹራንስ መንግሥት እንዲሸፍን በማድረግ፣ የመድሃኒት አቅርቦትንና ዋጋ ማሻሻል፤ በበሽታው ለተጠቁ የራስ መጠበቂያ ቁሳቁሶችንና በበሽታው በተጠቁ አካባቢዎች የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎችን አቅርቦት በማሻሻል፣ ህክምናና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ ሰርታለች።

የአስቸኳይ ጊዜ የቁሳቁስ ድጋፍ

የማምረት አቅም ግንባታ እንዲሰፋ በማድረግ፣ የማምረት አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ ተቋማትን በማደራጀት፣ በየአካባቢው ያለ አስመጪ ድርጅቶችን በመደገፍና፣ የድንበር ዘለል የኤሌክትሮኒክስ ንግድ መሠረተ ልማቶችን በማቀናጀት የህክምና መሳሪያዎችን እንዲያስገቡ በማድረግ የአቅርቦት ሥርዓቱን በአስተማማኝነት አሻሽላለች።


ዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ትብብርና መረጃ ማካፈል

የቻይና መንግሥት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከጃንዋሪ 3/2020 ጀምሮ በየቀኑ የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ጉዳዮችን ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ሪፖርት በማድረግ፤ የቫይረሱ ባዮሎጂካዊ ዓይነት (pathogen) ከታወቀበት ጃንዋሪ 7 ጀምሮ ደቂቅ ህዋስ (genome) እና የቫይረሱ ህዋስ አወቃቀሮች (genome sequence) ለዓለም ጤና ድርጅትና ለዓለምአቀፍ ማህበረሰብ አሳውቋል።የቻይና ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን (National Health Commission) የወረርሽኙን ሁኔታ በተመለከተ በየዕለቱ በማሳወቅና ስለአጣዲፊ ጉዳዮችም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዕለታዊ የፕሬስ ኮንፈረንስ ሰጥቷል።

የማህበረሰብ ዘመቻና አካባቢያዊ ተሳትፎዎች

የአደጋ ጊዜ ምላሽና የመከላከል ሥራዎችን የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማሳተፍ ማከናወን፣አካባቢያዊ የማህበረሰቡ አባላትም ራሳቸውን በመነጠልና ህዝባዊ መግባባት በመፍጠር ረገድ ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ፣ ስርጭቱን በበቂ መንገድ መግታት ችለዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ባለሙያዎችም ቻይና ሁሉንም የማህበረሰብ አካላት በሙሉ እንደ አንድ ማንቀሳቀስ መቻሉና ጠንካራ የፈጣን ምላሽ ሥርዓት መዘርጋት መቻሉ አዳዲስ በኮሮና ቫይረስ የሚጠቁ ታማሚዎች ቁጥር በስፋት እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ምሥክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡


መንግስት አሁንም ከሌላው ዓለም ወደ ቻይና አዳዲስ የቫይረስ ታማሚዎች (imported cases) ተበራክቶ ወረርሽኙ ድጋሚ እንዳይከሰት የሚያስችል ጥብቅ እርምጃዎችን አጠናክሮ ቀጥሏል።ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ሥራ የቻይና መንግሥት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በመመደብ፤ ከፍተኛ የባለሙያ ንቅናቄ በመፍጠርና ቁሳቁስ በማሰባሰብ እንዲሁም የጤና ፋሲሊቲ በመገንባት፣ የጥናትና ምርምር ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ጥያቄ 4. ቫይረሱን ለመከላከል ከቻይና መውሰድ ያለብን ተሞክሮ ምንድነው ?

ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ ከቻይና መማር የሚገባት በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡በቻይና በሽታው ሲከሰት የአዳዲስ ታማሚዎች ቁጥር በቀን 3000 የነበረ ሲሆን ከአንድ ወር በኋላ ወደ 200 ዝቅ ማድረግ ችላለች፡፡ ለዚህም ዋነኛው ተጠቃሽ ምክንያት ሀገሪቱ የማያወላዳ ፈጣንና መጠነ ሰፊ እርምጃ መውሰዷና የታመሙትን ሰዎች በፍጥነት ለይቶ ማቆያ ማስገባቷ ነው።

የቫይረሱ እንዳለባቸው ምልክት የሚያሳዩ ህመምተኞች ቁጥር በአጠቃላይ ሲታይ በጣም አነስተኛ ስለነበር በቅድሚያ ምልክቱ የታየባቸውን በፍጥነት ወደ ህክምና ማእከላት የማስገባት ሂደት ሀገሪቱ መከተሏ፣በሽተኛና ጤነኛው የሚደበላቅበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ቻይና የኦንላይን የምክር አገልግልትና የመድሀኒት ማዘዣ ሥርዓት መዘርጋት ችላለች፡፡

በሚያስገርም ፍጥነት ሁኔታ ሆስፒታሎችን ገንብታለች፤ እንደገና ባቋቋመቻቸው በርካታ ሆስፒታሎች የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን የለይቶ ማቆያ ማዕከላት በብዙ ቁጥር እንዲጨምሩ በማድረግ በሽዎች የሚቆጠሩ ታማሚዎችን ማስተናገድ መቻሉ ፤ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ በፍጥነት የኦንላይን ትምህርት እንዲጀመር አድርጋለች፡፡

መድሀኒትና ምግብ ለሚሊዮኖች በቤታቸው ደጃፍ የሚደርስበትን በጣም የተዋጣለት ሥርዓት ዘርግታ ሁለም ካለበት ሳይንቀሳቀስ መሠረታዊ ፍላጎቱ እንዲሟላ ማድረጓ፣ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እና ለታመሙት የሚደረግ ህክምና በተለየ መልኩ በነጻ እንዲሆን በማድረግ ታማሚዎች ለክፍያ ሳይጨነቁ ወደ ጤና ማዕከላት እንዲገቡ ማድረጓ፣ ሲቪል የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ቻይናዊያን ለዓለም በኮሮና ቫይረስ ትግል አስተምረዋል፡፡
ቻይና ከ40,000 በላይ ዶክተሮችና ነርሶችን ከዚህም አብዛኛው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጥ ኃይል አሰማርታ ኮሮናን ተዋግታለች፡፡የመንገድ ሥራ ሠራተኞች ሙቀት በመለካትና ምግብ በማመላለስ ተሳትፈዋል፡፡ የሆስፒታል እንግዳ ተቀባዮች ኢንፌክሽን በመከላከል ሥራ በማገዝ በጎ ፈቃደኞች በፍልሚያው ውስጥ ቀጥታ በመግባት ቻይናን እና ዓለምን ከቫይረሱ የመከላከል ሥራ መሥራታቸው፣ የተለያዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች በጥቂት የሰው ኃይል በመስራት፣ ከቤት ሆነው ሠራተኞች የዕለት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማድረግ፣ በየተራ ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ የመከላከል ሥራውን በከፍተኛ ሁኔታ ማገዛቸው ከቻይና ቢወሰድ የሚጠቅሙ ምክሮች እንደሆኑ ማየት ይቻላል።

ከዚህም አኳያ በኢትዮጵያ ፦

ጠንካራ የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት የህግ አስፈፃሚ አካላትን አቅም ማጎልበትና ማደራጀት፤የቅድመ-መከላከል ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ግንዛቤ መፍጠር፣ የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ማደራጀትና አስፈላጊውን የህክምና መርጃ ቁሳቁስ ከወዲሁ ማሟላት፤ ወቅታዊና አስፈሊጊ የሆኑ ስትራቴጂዎችን፣ዘዴዎችን (methods) እና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል፤ የተማከለ፣ ነፃና ግልፅ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማድረግ፤ ቫይረሱ ሲከሰትም ሳይረበሹ ወይም panic ሳያደርጉ አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት መስጠትና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው።

መንግሥትና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክር በጥልቅ ዲሲፕሊን መተግበርና በተቀናጀ እና በተደራጀ ሀገራዊ ስሜት ችግሩን ለመቅረፍ በአንድ ዓላማ በመረባረብ ቫይረሱ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ይቻላል።

ጥያቄ 5. ህብረተሰቡ ከዚህ ወረርሺኝ እራሱን እንዴት መከላከል አለበት ይላሉ ?

ህብረተሰቡ የግልንና የአካባቢውን ንፅህና (personal and environmental hygiene) በየዕለቱ መጠበቅ እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎችና መንግስት የሚሰጡትን መመሪያ በትኩረት መከታተልና መተግበር ይኖርበታል። በተለይም የመከላከል እርምጃዎችን ሳይዘናጉ መተግበር፣ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ፤ በየጊዜው የግል ንፅህና መጠበቅ፣ የሚቻለው መጠን እቤት መሆን፣ ከሁለም በላይ እርስ በርስ መደጋገፍና መተባበር ያስፈልጋል፡፡

ጥያቄ 6. የኢትዮያ መንግሥት ለቫይረሱ እየሰጠ ያለውን ምላሽ ወይም እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንዴት ያዩታል?

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ አበረታችና ተስፋ የሚሰጥ ነው። በእስካሁኑም ስለቫይረሱ ግንዛቤ ለመፍጠርና አስቀድሞ ለመከላከል ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት በተለይም ከጤና ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ከግል ባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት እንዲሁም አስፈሊጊውን የገንዘብና የህክምና መርጃ ቁሳቁሶችን (personal protective equipments) ለሟሟላት ከተለያዩ ሀገራት በተለይም ከቻይና መንግስት ጋር እያደረገ ያለው ትብብር በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው።

ሆኖም ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ የሚሰጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ያሉ በመሆናቸው፤ ከህግ አስፈፃሚው አካል ጋር የበለጠ ተቀናጅቶ መስራት ያስፈልጋል። ከቫይረሱ መገታት በኃላምና አሁንም በኢኮኖሚ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስና የዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጎልበት በጠላቅይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ እየተወሰዱ ያሉ ተነሣሽነቶች ሚደነቁ ተግባራት ናቸው፡፡
መንግሥት ይህን ችግር ብቻውን እንደማይወጣው ስለሚገነዘብ የሁሉም ሙሉ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡

ጥያቄ 7. በህብረተሰባችን ውስጥ ያለው ከፍተኛ መዘናጋትስ …?

የህብረተባችን መዘናጋት አሳሳቢና ለቫይረሱ መሰራጨት በር የሚከፍት ነው። ስለሆነም ህብረተሰቡ… ከላይ ጥያቄ ቁጥር 5 ለማብራራት እንደሞከርኩት ለዚህ ወረርሺኝ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል፡፡ይህም ሆኖ በመንግስትና በሚዲያ በኩል ሳያሰልሱ የመከላከያ መንገዶችን ማሳወቅ፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጠናከር፣ አስፈላጊ ሲሆን አስገዳጅና የተቀመጡ ክልከላዎችን የተላለፉትን በህግ እስከመጠየቅ የሚደርሱ እርምጃዎችን መውሰድ የግድ ይላል።

በሀገራችን በቫይረሱ የተያዘና የሞተ ሰው ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ ስለቫይረሱ ያለን ግምት እንዳያሳንሰውና መዘናጋት እንዳይኖር ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በአግባቡ ካልተጠነቀቅን ሌሎች ሀገሮች የገጠማቸውን ፈተና የመሸከም አቅማችን ደካማ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም አካላት ያለምንም መዘናጋት የተጀመረውን ሀገራዊ ንቅናቄ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡
======//=======

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም