በደቡብ ወሎ የመኽር አዝመራ ዝግጅት ስራ እየተካሔደ ነው

58

ደሴ (ኢዜአ) ሚያዚያ 25/2012 በደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሩ ከኮሮና ቫይረስ ራሱን በመጠበቅ 442 ሺህ ሄክታር መሬት በመኸር ለማልማት እንቅስቃሴ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ እንደገለፁት በዞኑ 442 ሺህ ሄክታር መሬት በመኸር እርሻ ልማት በመሸፈን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅትም  ከታቀደው መሬት ከግማሽ በላይ የሚሆነው  የእርሻ ማሳ እስከ ሁለተኛ ዙር የማረስና የማለስለስ ስራ በመከናወኑ ወቅቱን ጠብቆ ለመዝራት ዝግጁ ሆኗል ።

በዚህ ዓመት በሚካሄደው የመኸር ሰብል ልማት የሚሳተፉ ከ462 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችም ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ስራውን በጥንቃቄ እንዲያከናውኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

ለዚህም በየቀበሌው ለሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች የኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ ቀድሞ በማሟላት አርሶ አደሩን ቤት ለቤትና በማሳ እየሄዱ ትምህርት በመስጠትና ሌሎች ድጋፎችን እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል ።

በተለይም የወሎ አርሶ አደሮች እስከ አሁን ድረስ በነበረው ልምድ የዘርም ሆነ የሰብል መሰብሰብ  ስራውን የሚያከናውኑት በደቦ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ዓመት ግን ተሰባስቦ በአንድ ላይ መስራት እንደማይቻል ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ለመጭው የመኸር አዝመራ በዘር ከሚሸፈነው መሬት 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመሰብሰብ  ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል 435 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና 20 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር  ለማቅረብ ታቅዶ እስከ አሁን ፈጥነው ለሚዘሩ ሰብሎች አገልግሎት የሚውል 248 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ተሰራጭቷል።

በዞኑ አልፎ አልፎ የሚከሰተው የአንበጣ መንጋም በሰብል ላይ ጉዳት በማድረስ ምርት እንዳይቀንስ አርሶ አደሩና ባለሙያው ተቀናጅቶ ከወዲሁ የመከላከል ስራ ለማካሔድ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ።

በጃማ ወረዳ የ015 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለባቸው ሙክታር እንዳሉት በዘንድሮው የመኸር አዝመራ አንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸውን  በስንዴና በጤፍ ዘር ለመሸፈን ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ አዘጋጅተዋል።

በግብርና ባለሙያዎች የሚሰጡ አሰራሮችንና ግብዓቶችን በመጠቀም ከ35 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

አንድ ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ በቆሎና ቦለቄ ለመዝራት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በተንታ ወረዳ የ031 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይመር ኑርዬ ናቸው፡፡

የኮሮና በሽታ ወደ አገራችን በመግባቱ ራሳችንና ቤተሰባችን ለመጠበቅ ሲባል የዘንድሮው የእርሻ ስራ በተናጠል መከናወን እንዳለበት የግብርና ባለሙያዎች ቤት ለቤት እየተንቀሳቀሱ  ትምህርት እየሰጡን ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በመኸር ከለማው ከ441 ሺህ ሄክታር መሬት 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቶ እንደነበር ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም