ኢትዮጵያ የ1970ውን የዩኔስኮ ስምምነት መፈረሟ ተጠቃሚ ያደርጋታል

63
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 ኢትዮጵያ የዩኔስኮን ስምምነት መፈረሟ ለቅርስ ጥበቃና ማስመለስ እንቅስቃሴዋ ይረዳታል ተባለ። የቅርሶችን ደህንነት ለማስጠበቅ፣ ለማስመለስና ዓለም አቀፋዊ እውቅና ለማግኘት እ.አ.አ በ1970  የተፈረመው ስምምነት ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ተገልጿል። ስምምነቱ ባህላዊ ሃብቶች በህገወጥ መልኩ ወደ ማንኛውም አገር እንዳይገቡ፣ ከአገር እንዳይወጡና የራስ ላልሆነ ቅርስ ባለቤትነት መውሰድን ለመከላከል ታስቦ በ137 አገራት የተፈረመ ነው። በዩኔስኮ የቅርሶች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ የቅርስ አጠባበቅና አያያዝ፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ህጎች ላይ በዘርፉ ለሚሳተፉ አካላት የሚሰጠው የሶስት ቀን ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል። በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ዳይሬክተር አና ኤሊሳ ሳንታና በዚሁ ወቅት እንዳሉት "እ.አ.አ ከ1970 ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ አፍሪካ የቅርስ ዝርፊያና ህገወጥ ዝውውር ተጠቂ ሆናለች"። ኢትዮጵያም በዓለም ጥቂት የፅሁፍ መዛግብት ካለቸው አገራት አንዷና በአፍሪካም በልዩ ልዩ ባህላዊ ቅርሶቿ ቀዳሚ ብትሆንም ችግሩ ከሌላው በተለየ በስፋት እንደሚታይባት ገልፀዋል። በዚህም ሳቢያ "የማይተመን የቅርሶች ጉዳት" እየደረሰ ነው ብለዋል። ከዚህ አንፃር የሚሰጠው ስልጠና ጊዜውን የጠበቀና ኢትዮጵያም የምታደርገው እንቅስቃሴ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲያገኝ  የሚረዳ ነው ሲሉ ተናግረዋል። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የቅርሶች ምዝበራና ህገ-ወጥ ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ ይታያል ነው ያሉት። ዳይሬክተሩ አክለውም ችግሮቹን ለመከላከል ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብላ ከማፅደቅ ባለፈ የቅርስ ምዝገባ የመረጃ ቋት አዘጋጅታ ማስመረቋን ጠቁመዋል። እ.አ.አ በ1973 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት  በተካሄደው አጠቃላይ ጉባኤ የራስ ያልሆነን ባህላዊ ሃብት ለማስመለስ አቋም ቢያዝም ኢትዮጵያን እንዳልጠቀማት ገልፀው፤ ሁለቱን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት በማድረግ በቅርስ ማስመለስ ላይ ፍትህ እንዲሰጣት እንደምትፈልግ ገልፀዋል። በተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ ባለ የመረጃና የማረጋገጫ እጥረትም ብዙ ቅርሶች ከአገር ወጥተዋል ነው ያሉት። ስልጠናው ከአገሪቷ የተዘረፉ ቅርሶችን በመረጃ ለይቶ ተገቢውን ጥያቄ ለማቅረብ ከማስቻሉም ባለፈ ያሉትንም ቅርሶች በአግባቡ መዝግቦ እውቅና ለማግኘት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያግዝ አስረድተዋል። በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ የተመዘበሩ ቅርሶች በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካና በእስያ እንደሚገኙና ቅርሶቹን ለማስመለስ እየተደረገ ያለውን ጥረትም በተለይ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ በእጅጉ ማገዝ  እነዳለበት ገለጸዋል። የእንግሊዝ ሁለት ሙዚየሞች የኢትዮጵያን ቅርሶች በረጅም ጊዜ  እንመልሳለን ያሉትን ሃሳብ ኢትዮጵያ የማትቀበለው መሆኑን ገልጸው በድርድር ሙሉ ለሙሉ ለማስመለስ እንደምትሰራም ገልጸዋል። በአሁኑ  ሰዓት በዓለም ላይ ከህገ-ወጥ የሰዎችና የእፆች ዝውውር ቀጥሎ የቅርሶች ህገ-ወጥ ዝርፊያና ዝውውር ከፍተኛ ቦታ ይዟል። የተባበሩት መንግስታት እ.አ.አ በ2030 ዘላቂ የእድገት ግቦቹ ቅርሶችን በመጠበቅ ስራን መፍጠር፣ ጾታዊ እኩልነት ማረጋገጥና ድህነትን ለመቀነስ አልሞ እየሰራ ይገኛል። የባህል ኢንዱስትሪዎች በዓመት ሰባት በመቶ የዓለም ኢኮኖሚ ድርሻ እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም