በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የአምስት ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዙ

59
አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2010 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የአምስት ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ መፈጸማቸው ተገለጸ። ኢትዮጵያዊያኑ ግዢውን የፈጸሙት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ሰባተኛ ዓመት በዱባይ ሲከበር ነው። በዱባይ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ዳይሬክተር ወይዘሮ ኢየሩሳሌም ዓምደማሪያምን በዓሉ በተከበረበት ወቅት እንዳሉት፤ በዱባይና በኤምሬቶች ነዋሪ ኢትዮጵያውያን የፈጸሙት ቦንድ ግዢ ለአገራቸው ልማት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡበት ተግባር ነው። በዱባይና በሰሜን ኤምሬቶች የታላቁ  ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዑስማን አብዱ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያኑ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉት ድጋፍ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። ነዋሪዎቹ በዕለቱ የፈጸሙት ግዢ የቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ተግባራቸውን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተናግረዋል። በዕለቱ በበዓሉ አከባበር ላይ ለተገኙ ኢትዮጵያውያን ስለ ግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ደረጃ ገለጻ ተደርጓል። ቦንድ ለገዙና ድጋፍ ላደረጉም ምስጋና የቀረበ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም